በእውነት ወያኔ ምን በደለ ? እንደው ሀገር ባለማ ! ድልድይ በሰራ ፣ ግድብ በቆፈረ ! ውይ የሰው ነገር ! አሁን ማን ይሙት ወያኔ የደርግን ያህል ጨካኝ ሆኖ ነው እንዲህ የምትረባረቡበት ? እናንተ እኮ አታፍሩም ይሄኔ ፣ ከግድብ የመናገር ነጻነት ይቅደም ፣ ከውሃ ማቆር የሰው ልጆች እኩልነት ይቅደም ፣ ከልማታዊ አርሶ አደርነት የሰብአዊ ክብር ና የመንፈስ ልዕልና ይቅደም ፣ የተጻፈ ከማንበብ ( ዘላለማዊ ክብር ለክቡር ጥቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ የሚለውን አይነት ማለት ነው ) የመጻፍ መብት ይከበር ፣ በየመንገዱ ሥራ አጥቶ ከመደርደር ፣ የመሰለፍ መብታችን እውቅና ይሰጠው ፣ አስራ አራት ክልል በካርታ ላይ ከማስቀመጥ ፣ በፈለግነው ክልል ሄዶ የመስራት መብታችን ይጠበቅ ፣ የዜጎች እኩልነት በዜና እና በዝና ሳይሆን በነባራዊው ዓለም ፣ በለት ተለት ሕይወታችን ይተግበር እና ወዘተ ትሉ ይሆናል ።
በእውነት አታፍሩም ! አሁን እስኪ ማን ይሙት ፣ ድልድይ ይበልጣል ፣ የህዝቦች እኩልነት ? ለኛ የመጻፍ ነጻነት ይሻለናል ወይስ የማቃጠር መብት ? ዜጎች ደሞ እኩልነት ፣ እኩልነት ፣ እያላችሁ የምታላዝኑት ፣ እንኳንስ ይቅርና በዜግነት መብት በቁመት እኩል የሆኑ ሰዎች ማግኘት ዘንድሮ ቀላል ነገር ነው ወይ ? ደሞ በተወደደ ወረቀት መጻፍ ፣ መጻፍ ፣ መጻፍ ። አማራ ድሮም መጻፍ ይወዳል ! ክስ ይወዳል! ምናለ ባትጽፉ አትሞቱ ፣ እውነት ባትናገሩ አትሞቱ ፣ ስለ ሚኒሊክ ባትናገሩ አትሞቱ ፣ ስለ በላይ ዘለቀ ባታወሩ አትሞቱ ! አሁን የደደቢት ታሪክ አልበቃ ብሎ ነው አዳሜ የ አጼ ቴዎድሮስን ታሪክ የሙጥኝ ያለው ? አረ ምን እሱ ብቻ ፣ ሀገር ፣ ሀገር ፣ ሀገር ትላላችሁ ? ሀገር ምንድን ነው ? ባንዲራ ፣ ባንዲራ ፣ ባንዲራ ? ባንዲራ ድልድይ አይሆን ? ምንነት አይበላ ! ነጻነት አይሸጥ ። ይህ የአማራ ተረት ነው ። አሁን እስኪ ማን ይሙት ለኢትዮጵያ የሚጠቅማት ኮብል ስቶን ነው ወይስ አክትቪስት ? “እኛ ( ወያኔ-ትግሬዎች ) እኩል ሳትሆኑ እኩል አደረግናችሁ ፣ ከጨቋኝ ፊውዳል እጅ ታደግናችሁ ፣ ዛሬ በራሳችሁ ቋንቋ መናገር ስትችሉ ፣ የፈቀዳችሁትን ባንዲራ አወጣችሁ ፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብት ያለገደብ ተከበረ ፣ ታዲያ ይሄም አልበቃም ብሏችሁ ፣ እኛ ታግለን ባመጣነው ፣ ስልጣን ላይ መቀመጥ አማራችሁ ? ” ።
ታዲያ ለምንድን ነው ይህን ” ደሙ ሰጥቶ፣ አጥንቱን ከስክሶ ፣ የስኬት ማማ ላይ ያስቀመጣችሁ ጀግና ስርዓት የምትፈታተኑት ? ” ተዉ ግን ፣ ተው ? እኔ ልሙት አሁን የወያኔ ጥፋቱ ምኑ ላይ ነው ? ይሄኔ እኮ << ምርጫ 100% አሸነፈ ፣ ነብዩን ገደለ ፣ የእስልምና ኮምቴዎችን አሰረ ፣ በስልጣን ላይ ያሉት አብዛኛው ካንድ ብሔር የተመረጡ ናቸው ፣ በዘር ተደራጅተው ሀገሪቷን ተቀራመቷት ፣ ወያኔ እጁ ላይ ደም አለ ፣ መንግስት ሳይሆን ቃሊቲ ( ዘብጥያ ) መውረድ ያለበት ስርዓት ነው ፣ ይህ ስርዓት ቢያንስ የቃልቻ ያህል እንኳ ለሀገር ሰላም አይጸልይም ፣ ይህ ስርዓት ሳይሆን የእባብ ስሪት ነው ” እና ወዘተ ትሉ ይሆናል ። ቆይ ቆይ << 17 ዓመት የታገለ ስርዓት አንድ ነብዩን ቢገል ምን አለበት ፣ ሀገር በማልማት ላይ ያለ መንግስት ፣ የህዝቡን ድምጽ ቢሰርቅ ምን አለበት ? ቆይ አሁን አባይን እየገነባ ያለ ኃይል ፣ መጅሊስን ቢያፈርስ ያን ያህል መጅሊስ ትልቅ ነገር ሆኖ ነው ፣ እንኳን መጅሊስ << ቲዊን-ታወር ፈርሶ የለም እንዴ ? >> ። ደሞ- መጅሊስ መጅሊስ አትበሉ ፣ በየሰፈሩ ህውሃት መጅሊስ አረቢ አስነጥፎ ሺሻ ያለገደብ እንዲገባ ያደረገውን ረስታችሁ ነው ስለሌላው መጅሊስ የምታወሩት ? ምን ታካብዳላችሁ ? ደሞ ተቃዋሚ የምትባሉት ሁሉ ትልቁ ችግራችሁ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ ? ትልቁ ችግራችሁ ንገረኝ ካላችሁ << ወሬኞች ናችሁ !>> እኛ ደሞ በወሬ አንፈታም ። አንድም ቆራጥ በመሃከላችሁ የለም ! <<ፈሳም ሁላ !! >> << ወያኔ እንዳንቺ አማሪካን ሀገር በርገር እየበላች መሰለሽ ስልጣን ላይ የወጣችው ? ታግላ ነው ፣ ከገባሽ >> ደሞ እኛ ልማት ላይ ነን ! አንቺን የሚያስጨንቅሽ ያንድ ጋዜጠኛ መሞት ነው አይደል ? እኛን የሚያስጨንቀን ግን ያርማታ ሙሌት ነው ? አንቺ እስክንድር ለምን ታሰረ የሚለው ነው አይደል እንቅልፍ የሚነሳሽ ? እኛን ወያኔዎችን እንቅልፍ የሚነሳን የሲሚንቶው መቡካት ወይም አለመቡካት ነው ፣ እኛን የሚያስጨንቀን የአበባ እርሻው ነው ፣ እኛን የሚያስጨንቀን የኦባማ በሰላም ወጥቶ መግባት ነው ፣ እኛ የልማት ኃይሎች ነን ። አሁን አንድ አቡበከር ተፈታ አልተፈታ ለኢትዮጵያ ምን ይጠቅማታል ? ከገባሽ እኛን የሚያስጨንቀን እንዴት ለቀጣዩ 100 ዓመት ያለ ተቀናቃኝ እንደምንገዛሽ ነው ።
አሁን እስኪ ማን ይሙት ወያኔን የመሰለ ስርዓት በኢትዮጵያ ምድር ተፈጥሮ ያውቃል? አንድ ዘር ፣ አንድ ዘር የምትሉት ደሞ ትግሬ ስለምትጠሉ ነው እንጂ ፣ ትግሬ ቢገዛ ምን አለበት ? ትግሬ ምን አረገ ? እኛ ከዘረኛ አማራ አድነናችሁ ፣ ትግሬ ፣ ትግሬ ትላላችሁ ? ደሞ ስልጣኑ አይ ማን ነው ያለው ? ሃይለማርያም ትግሬ ነው ? ነጋሶ ገዳዳ ትግሬ ነበር ? ግርማ ወልደጊዮርጊስ ትግሬ ነው ? ደመቀ መኮንን ትግሬ ነው ? አንድ ትግሬ ስልጣን ላይ የነበረ መለስ ብቻ ነበር ፣፣ እሱም በጭንቅላቱ ነው ፣ አሁን ደሞ እሱ ሞተላችሁ ( ሞቶም አልተዋችሁትም እንጂ !) ፣ ሃይለማርያም ጠቃላይ ሚኒስትር ሲሆን ደሞ ምን እንደምትሉ እናያለን ዘረኞች ! ስለ ጀነራሎች የምታወሩት ደሞ እኮ ፣ እነሱ ታግለው ነው ፣ ለ 17 ዓመት አፈር በልተው ፣ ታዲያ አንድ ባለ እስክርቢቶ አማራ መጥቶ ይውሰደው ? ደርግ ይምጣ እና ይግዛን ነው የምትሉት ? ይልቅ አንዳንድ ጥቃቅን ስህተቶች ይኖራሉ ፣ እነሱም በሂደት የሚስተካከሉ ናቸው ። እኛ በዲሞክራሲ ስርዓት ላይ መጏዝ ከጀመርን ገና 25 አመታችን ነው ። ዲሞክራሲ ምን እንደነበር ለማያውቅ ሕዝብ ፣ ሁሉንም ባንዴ ብንፈቅድለት ቀስ እያልን እናድርገው ብለን ነው ፣ ደሞ እናንተስ እንኳን የኛን ዲሞክራሲ ፣ የባቄላ ፈስ በቅጡ መቆጣጠር የሚችል መቀመጫ ሳይኖራችሁ ዘላችሁ ወንበር ላይ ቁብ ማለት ምን የሚሉት ችኮላ ነው ።
አንዳንድ ሽብርተኞች ፣ ህገ መንግስቱን ለመናድ ከውጭ ኃይሎች እና ሰርጎ ገቦች ጋ በማበር ፣ ድርጅታችን ኢህአዲግ ቀን ከሌት ፣ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል እየተጋበት ያለውን የወደ ልማት ጎዳና ባጭር ለመቅጨት ቢሞክሩም ፣ የድርጅታችንን አላማ በተረዱና ፣ በድርጅታችን ላይ ላለፉት ሃያ አመታት ትልቅ እምነት በጣሉ ግለሰቦች ( በግል ተነሳሽነት ) ይህ የወንጀል ተግባር በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል ። ከዚህም ውስጥ እንደምሳሌ የዚህ የሽብር ቡድኑ መሪ እና ዋነኛ ተዋናይ የነበረውን ሰው ( አንዳርጋቸው ጽጌ ) በቁጥጥር ስር አውለናል ። ያም ቢሆን ድርጅታችን ፣ አንዳርጋቸው ለመጽሐፍ ያለው ፍቅር ፣ የኛን የባለ ራዓዩን ጠቅላይ ሚንስትር ፍቅር ስላስታወሰን ፣ በራሳችን ተነሳሽነት ፣ ሙሉ ወጪውን ሸፍነን << አንዳርጋቸው ሆይ ኤርትራ ውስጥ ቦምብ ከምታፈነዳ ፣ እዚህ እኛ ጋ መጽሐፍ አሳትም >> ብለነው ፣ እሱም ምክራችንን ተቀብሎ መጽሐፍ እየጻፈ ነው ። ካላመናችሁ ጠይቁት ፣ እንደውም ዛሬ ገጽ 180ን ጽፎ ጨረሰ ! እንዴትም ብሎ ለጉምቦት ሃያ አለበለዚያ ለባዕለ የካቲት ወይም ፓርላማ ተመርቆ ከመከፈቱ አንድ ሳምንት በፊት ለአንባብያን እንደሚደርስ በዚህ አጋጣሚ መግልጽ እንፈልጋለን ።
እና አባካችሁ ፣ ይህን ” ደሙን ሰጥቶ፣ አጥንቱን ከስክሶ ፣ የስኬት ማማ ላይ ያስቀመጣችሁ ጀግና ስርዓት አትፈታተኑት ! አረ ተው ታማኝ ተመከር ! አሁን ወያኔን አሜን ብለህ ብትቀበል እኮ፣ እንደ ንዋይ ደበበ ጥሬ ስጋ ስትበላ ፎቶ ተነስተህ ትለጥፍ ነበር ፣ ደደቢት ታንክ ላይ ሆነህ ፎቶ ትነሳ ነበር ፣ ከፈለካት አይነት ሴት ጋ እንደፍለክ ትሆን ነበር ፣ አንተ ግን ዝም ብለህ ነጻነት ፣ እኩልነት ፣ የህዝቦች መብት እና ወዘተ ትላለህ ። ህዝቡ ራሱ ( በብላሽ !) ፣ በኪሳራ ነው ኑሮውን ለባርነት ፣ ህይወቱን ለጭቆኛ አሳልፎ የሰጠው ። ታዲያ አንተ ምን አገባህ ! ? ይልቅ እንደ ሰለሞን ተካልኝ ፣ ለጥሬ ስጋ ስትል ሀገርህ ላይ ፣ ለቀይ ወጥ ስትል ሕዝብህ ላይ ፣ ለሆድህ ስትል እውነትህ ላይ ተገልብጠህ ፣ የቀበሌ ስብሰባ መጥሪያ ” ሃሎ- ሃሎ ” ይዘህ ” ትናንት አንድ በሉ ፣ እሪ በል ቦሌ እሪ በል ፒያሳ ” ባልክበት ጉሮርሮህ ” ቅንድቡ ፣ እጁ ፣ አይኑ ፣ አፍንጫው” እያልክ ብትዘፍን አይሻልም ? አረ ተው ታማኝ ! አረ ተው !
አሁን አበበ ገላው ታላቁ መሪያችን ላይ ፣ ሊያውም በዓለም አደባባይ ፣ ትላልቅ ሰዎች በተገኙበት ፣ እንደዚያ መጮህ ነበረበት ? ማን ተዋረደ ? አበበብ ራሱ ! ያንን የሚያህል አስተዋይ መሪ ያዋረደ መስሎት ፣ ተሳስቷል !
አና አሁንም እኛ ልማት ላይ ነን
ከሰው ሕይወት የድንጋይ ቁመት የማረከን
እኛ አለታውያን
እኛ ኮንክርታውያን
እኛ ድልድያውያን
ከሀገር ውርደት የኛ ሆድ የበለጠብን
ከህዝብ ክብር ፣ ንዋይ እንደ ኩይሳ የደም ሲሳይ የጫነብን
ከነጻነት እና ፍቅር ፣ ጥላቻ መንገድ የሰራብን
የጥፋት ልማተኞች
የክፋት መንገደኞች
በሰው ደም የሰከርን
በአልኮል የሰከርን
በጥላቻ የሰከርን
ይህንንም በ 100 % ምርጫ ውጤት ያስመሰከርን
አስክሬኖች ነን
እና ታዲያ ምን አረግን ?
ተው ፣ አረ ተው ፣ ይህንን ” ደሙን ሰጥቶ፣ አጥንቱን ከስክሶ ፣ የስኬት ማማ ላይ ያስቀመጣችሁ ጀግና ስርዓት አትፈታተኑት !