Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » News
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2784

ሀገራዊ የጸሎት ጥሪ -ሰሎሞን ንጉሡ (ከሱዳን)

$
0
0

ሰሎሞን ንጉሡ (ከሱዳን)  (የካቲት 11 ቀን 2007ዓ.ም ተጻፈ)
prayerእንዴትና በምን አኳኋን ይህን የጸሎት ጥሪ እንደምጀምር ጭንቅ ብሎኝ በጣም ግራ ተጋብቼ ነበር፡፡ ልጻፍ አልጻፍን ጨምሮ ከራሴ ጋር ብዙ ተሟገትኩ፤ “ጊዜው ገና ነው” በሚልም ጭምር፡፡ ለማንኛውም አፍ ወድቆ አይሰበርምና መጻፌ ካለመጻፌ እንደሚሻል ራሴን አሳመንኩ፡፡ ደግሞም ለማንኛውም ራሴን በትንሹ ማስተዋወቁ ለጸሎት ጥሪዬ መጠነኛ ትኩረት ያስገኝልኝ ይሆናል የሚል ተስፋ አሣደረብኝ፡፡ አንባቢያንም – ለማንኛውም – ይህን የጸሎት ጥሪ ችላ ሳትሉ ዐይንና ጆሮ ላላቸው ኢትዮጵያውያን ሁሉ በምታገኙት አጋጣሚና ባላችሁ የመገናኛ አውታር አድርሱልኝ፡፡ በተረፈ ሊሆን ያለው ሁሉ ከመሆን እንደማይዘለል ብዙዎቻችን ስለምናምን በተለይ የሀገራችንን ነፃነት በሚመለከት በየበኩላችን የምንችለውን ከማድረግ ውጪ በህልም ዓለም ሩጫ በከንቱ ልንባዝን እንደማይጠበቅብንና እንደማይገባንም ባስታውስ ቅር የሚለው ሰው አይኖርም ብዬ እገምታለሁ፡፡

የደርግ መንግሥት ሊወድቅ ጫፍ ላይ ነበር፡፡ ያኔ በ82 እና በ83ዓ.ም ሀገር ልትፈራርስ አንድ ሐሙስ ቀርቷት በነበረበት የኤሎሄ ሰዓት ሕዝቡ በደርጎች ላይ በነበረው ከፍተኛ ጥላቻ ምክንያት የወያኔዎች ግስጋሴ ከቁብም አልተቆጠረም ነበር፡፡ የደርግ ጨፍጫፊነትና አረመኔያዊ አገዛዝ የወያኔዎችን የትግል እንቅስቃሴ አልጋ ባልጋ አደረገው፡፡ ብዙዎች “ከደርግ የማይሻል አይመጣም” ከሚል ተላላነት የተነሣ ለወያኔዎች መልካም ፊት ከማሣየት ጀምሮ ሁለንተናዊ እገዛም የሚያደርገው ገራገር ዜጋ ጥቂት አልነበረም፡፡ የነሴኩቱሮ የጫካ ፕሮፓጋንዳም ቀላል አልነበረም፡፡ ለብዙኃን የዋሆች በቀላል መሸነፍ ምክንያት የነበረው የወያኔዎች ሥልታዊ የቆረጣ ፕሮፓጋንዳና የደርግን ጦርና መንግሥት በልዩ ልዩ ዘዴ ከፋፍሎ የማሽመድመድ መሠሪ ተንኮል ነበር (ለትግሬው አድማጭ፣ ለአማርኛው አድማጭ፣ ለኦሮሞው አድማጭ፣… የተለያዬና እርስ በርስ የሚጋጭ ቅስቀሳ እንደነበራቸው ያስታውሷል)፡፡ ያኔ ነበር ታዲያ በወቅቱ የወያኔ ሤራ ከሚያንገበግባቸው ከነገብረ መድኅን አርአያና አብርሃም ያዬህ ያልተሣካ ሀገርን የማዳን ጥሪ ጩኸት ቀጥሎ እኔም የአቅሜን በዚህ ብዕር የተፍጨረጨርኩት፡፡ የታሪክ ሽሚያ ውስጥ መግባቴ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ፤ በፍጹም፡፡ እዚያ ውስጥ የመግባት ዓላማም ሆነ ፍላጎት የለኝም፡፡ አንዳንዶች ይህን ስም ስታዩ የሚቀሰቀስባችሁን ትዝታ ብጋራ ግን አልጠላም፡፡

የወያኔን ጉድፍና ሀገርን የማጥፋት ዘመቻ ብቻ ሣይሆን የደርግ መንግስት ራሱና በውስጡ የተሰገሰጉ አፍራሽ ኃይሎች ያደርጉት የነበረውን በደል በቅን ልቦና በመነሣት በጽሑፎቼ ውስጥ አካትት ስለነበር የተወሰነ ተሰሚነት የነበረው ብዕር እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በእውነቱ በዚያን ዘመን ለአቅመ-ፖለቲካ የደረሳችሁና ለሚዲያ ቅርበት የነበራችሁ እንደምታስታውሱት ስለወያኔዎች በጋዜጣም ይሁን በሬዲዮና በቲቪ ያልቀባጠርኩት አልነበረም፡፡ ብዙ ሥፍራዎችን እየተቆጣጠሩ ስለነበርና ከሚይዟቸው አካባቢዎች የመረጃ ምንጭ ስለነበረኝ እነዚህ ብልሹ ዜጎች ሀገራችንን ወዴት አቅጣጫ ሊወስዷት ይቋምጡ እንደነበር የበኩሌን ገልጫለሁ፡፡ የብዙዎቻችን ጩኸት ግን የቁራ ጩኸት ሆኖ ነው የቀረው፡፡

ከሁለት አሠርት ዓመታ ፀጥታ በኋላ ታዲያ ምን መለሰኝ?

እንደነገርኳችሁ ያኔ እኔን ጨምሮ የወደፊቱ እሳት አስቀድሞ የታያቸው ወገኖች ብዙ ጮኹ፡፡ እንደምናስታውሰው ያዳመጣቸው ግን አልነበረም፡፡ የሞኙ እረኛ ዓይነት ክስተት ተፈጠረና ቀድሞ የተነገረው ነገር ግን ማንም ከቁም ነገር ያልቆጠረው የወያኔዎች ሤራ ተግባር ላይ ሲውል ልቅሶውና ዋይታው በረታ፡፡ እንደተባለውም ሀገር ድምጥማጧ ጠፋ፡፡ አይሆንም የተባለው ሆነ፤ ይሆናል የተባለው ሣይሆን ቀረ፡፡ የዘረኝነት ክርፋቱ፣ የሞራል ዝቅጠቱ፣ የሃይማኖት መላላቱና ለአምልኮተ ንዋይ መንበርከኩ፣ የሙስና መንሠራፋቱ፣ ከሞላ ጎደል ሁሉም የሀገሪቱ ቋሚና ተንቀሣቃሽ አንጠራ ሀብት በሕወሓት ቁጥጥር ሥር መግባቱ፣ በማይማንና ደናቁርት ዘረኞች መገዛቱ፣ በኢትዮጵያዊነት ሰበብ ስቃይና እንግልቱ አለቅጥ መስፋፋቱ፣ በትምህርት ረገድ ከሞላ ጎደል በሁሉም የትምህርት መስክ ቁልቁል መንጎዱና የበታችነት ስሜት የሚያስከትለውን አእምሯዊ ምስቅልቅል ለመሸፈን የውሸት ዲግሪ በመንግሥት መሪዎች ዘንድ ሣይቀር እንደዘመናዊ ፋሽን መዘውተሩ፣ ውሸትና ቅጥፈት የመንግሥት መርህ ሆኖ ሥራ ላይ መዋሉ፣ አንድን የኅብረተሰብ ክፍል ለይቶ ከማንኛውም የሀገሪቱ የጥቅም ቦታዎች ማስወገድ ብቻ ሣይሆን ዘሩም እንዳይተርፍ በያለበት ማሳደዱና መቀጥቀጡ ወዘተ. በሀገራችን በግልጽ ታዬ፡፡ የሀገሬን ውድመት መጀመሪያውን ያሣየኝ የኢትዮጵያ አምላክ አሁን ደግሞ የጠላቶቿን የመጨረሻ አይወድቁ አወዳደቅ ሊያሣየኝ ዳር ዳር እያለ መሆኑን ስድስተኛው የስሜት ሕዋሴ ሹክ አለኝና ዛሬ ተመለስኩ፡፡ የሰቀልኩትን ብዕርም አቧራውን አራግፌ ይሄውና አሃዱ አልኩ፤ ጥፋት አይመስለኝም፡፡

“መካሪ የሌለው ንጉሥ ካለአንድ ዓመት አይነግሥ” የሚለው ብሂል ትርጉም ካጣ ሰነበተ፡፡ ይሄውና 24 ዓመትም ቢሆን መንገሥ ተችሏልና፡፡ 24 ብቻም አይደለም፡፡ በጥቅሉ 40 መሆኑ ነው፡፡ አሥራ አንድም ይሁኑ በመቶ ሺዎችም ይቆጠሩ ዋናው የመከራችን ድግስ ከተጠነሰሰባት ከዚያች ከቀኖች ሁሉ ተለይታ ልትረግም ከሚገባት የካቲት 11/67 ጀምረን በነሱ የቅዠት ዓላማ ሥር ወድቀናልና የሰቆቃ ዘመናችን 40 ዓመቱን ደፈነ፡፡ የዚህ ዘመን አበቅቴም ያለቀ ይመስለኛል – ልንገባባቸው ከማያስፈልጉን ብዙ ነገሮች አንጻርም ቢሆን፡፡

እንግዲህ የወያኔ ዘመን አልቋል የሚለውን በጋራ የምንስማማበት ሃሳብ እንዲሆን ምኞቴ መሆኑን ልግለጽና ወደ ጀመርኩት የጸሎት ጉዳይ ወደሚያመራኝ መንደርደሪያ ልግባ፡፡

አሁን በዓለም ዙሪያ እየሆነ ያለውን የአረመኔነት ተግባር ሁሉ ተመለከትኩ፡፡ በተለይም ሰሞነኛ ስለሆነው ዘግናኝ የአይሲሎች ጉዳይ ሲነሣ የማይደመም ከንፈሩንም የማይነክስ የለም፡፡ በበኩሌ የሰው ልጅ በሰው ልጅ ላይ የሚፈጽማቸው እነዚህን መሰል አሰቃቂ ግፎች ከዘመን መጨረሻ ትንቢቶች ጋር (endtime predictions) ይያያዙ እንደሆን በሚል ጥቂት ድረገፃዊ መዛግብትን ለማገላበጥ ሞክሬያለሁ፡፡ ዝርዝሩ በርካታ ስለሚሆን ወደዚያ መግባት አያስፈልግም፡፡ ኹነቶችን  መመርመርና የዘመን አሻራዎችን በማጤን የትኛው ከየትኛው በምን እንደሚለይ፣ የትኛው ድርጊት ለየትኛው ቀዳሚ ትንቢት ጠቋሚ ሊሆን እንደሚችል ማስተዋሉ ግን መጥፎ አይመስለኝም፡፡

የክፋት ድርጊቶች አፈጻጸማቸው ቢለያይም ዓላማና ግባቸው ግን ተመሣሣይ ነው፡፡ አንዱ ወገን ከሃይማታኖዊ ቀኖናው ተነስቶ ሊፈጽመው ይችላል፤ ሌላኛው ወገን ከአለማወቅ ተነስቶ ሊፈጽማቸው ይችላል፤ አንደኛው በጠባብነት የዘረኝነት መነጽር አጮልቆ እየተመለከተ ከራሱ ዘር ውጪ ያለውንም ሁሉ እንደጠላትና የደኅንነት ሥጋት እየቆጠረ ከዚያ አኳያ ተነስቶ ሊፈጽማቸው ይችላል፤ ሌላው ደግሞ ከፍርሀት ተነስቶ ሊያከናውናቸው ይችላል፤ አንዱ ከኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኅልውና ሥጋት አንጻር በመነሣት ሊፈጽማቸው ይችላል፤ ሌላው ከበታችነት ስሜት ተነስቶ አገኘሁት ብሎ የሚያስበውን ጊዜ ወለድ ዕድል ላለማጣት ሲል ሊፈጽማቸው ይችላል፡፡ በ“የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” ባላዊ ፍልስፍና ከተመለከትነው በምንም ምክንያት ይፈጽማቸው ክፋቱ ግን ያው ክፋት ነው፡፡ የኃጢኣት ትንሽና ትልቅ ደግሞ የለውም፡፡ የወንጀልም እንዲሁ ይመስለኛል፡፡ ቅጣቱ ይለያይ እንጂ ኃጢኣት ኃጢኣት ነው፤ ወንጀልም ወንጀል፡፡ ‹አነሳም አንጠለጠለም ያው ተሸከመ ነው›፡፡

ወደ አፈጻጸሙ ስንመጣ ለምሣሌ አይስሎች ከአምልኮታቸው አንጻርም ሊሆን ይችላል – የክፋት ድርጊታቸውን የሚፈጽሙት የሚገድሏቸውን ሰዎች ብርቱካናማ ልብስ አልብሰው በማንበርከክ ጥቁር ጭምብል በለበሰ አራጅ አንገታቸውን በመቅላት ነው፡፡ እነሱንና ፈጣሪያችን ነው የሚሉትን ኃይል የሚያስደስቱበት መንገድ ያ ነው ማለት ነው፡፡ ምክንታዊነት፣ ተጠየቃዊነት ቅብጥርስ እዚህ ላይ አይሠራም፡፡ እዚህ መታወስ ያለበት የሚመስለኝ ተገዳዮች ንጹሓን ዜጎች መሆን አለባቸው፤ ወንጀለኞች ከሆኑ ገዳዮች ትኩረትንና ተፈሪነትን አያገኙም፡፡ በአገዳደሉ ብንከፋም መገደሉ የሚያስደስተን እንኖራለንና፡፡

በተመሣሣይ ሁኔታ በሀገራችን የአይስሊዝምን የአረመኔነት እምነት አቀንቃኞችን – ወያኔዎችን ማለቴ ነው –  ብንመለከት ክፋቱና የክፋቱ የሩቅ ግብ አንድ ነው፡፡ አንድን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የኃይል እርምጃን በመውሰድ መፈራትና ፍርሀትን የርዕዮተ ዓለም ማራመጃ ማድረግ ነው፡፡ ወያኔዎችም ሆኑ ቢጤዎቻቸው የሚያደርጉት ነገር መልካም እንዳልሆነ እነሱ ራሳቸውም ያውቁታል፡፡ ግን ሌላ መንገድ እንደማያዋጣቸው ደግሞ እነሱም እኛም እንረዳለን፡፡ አይስሎች በማስፈራራት ጭራቅ መስለው መታየትን የወደዱት ፈልገውት ሣይሆን የአስተሳሰብ ትንሽነት(ድውይነትም ቢባል ያስኬዳል) የሚፈጥረውን የበታችነት ስሜት ለማስወገድ ጭካኔን እንደሀሽሽ በመጠቀም ብዙኃንን ማርበድበድና ሥጋን ብቻ ሣይሆን ነፍስንም ጭምር በነሱ ሥር ለማንበርከክ መሞከር ነው፡፡ ሠላሣ ምናምን ሺህ የኢስላሚክ ካሊፌት ተብዬዎቹ ጦር በብዙ ሚሊዮን ለሚቆጠረው  የዓለም ሀገሮች ጦር ሠራዊት ቢከፋፈል ለቁርስነት እንኳን ፈጽሞ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ምንም ያህል ቁጥር ይኑረው – ወያኔ ይተማመንበታል የሚባለው የሕወሓት ዘውድ ጠባቂ ጦር ሠራዊት ለጭቁኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቢከፋፈል – ለአያ ፍርሀት ምሥጋና ይግባው እንጂ – ለቁርስ ቀርቶ ለአፍ ማሟሻ መክሰስ ቢጤ እንኳን አይሆንም፡፡ ይህን የወያኔ ውስጣዊ የአመለካከት/የአስተሳሰብ ትንሽነትና የጥቂትነት ስሜት እስከተቻለ ድረስ በዘለቄታ ለማቆየት ፍርሀትን ከማንገሥ ውጪ ያለው አማራጭ እስከዚህም ነው፡፡ በፍቅር ሁሉን አስተሳስረው እንዳይገዙ ከጉልበትና ከእልህ ውጪ ዕውቀትና ጥበብ የላቸውም፡፡ ምርጫ ከተባለ ደግሞ መቼም ቢሆን ገዳይህን ይግዛኝ ብለህ አትመርጥምና አያስኬዳቸውም፡፡ ያላቸው ብቸኛ መንገድ ምርጫን በማጭበርበር “የዓለምን ማኅበረሰብ” ማታለል – የውስጥ ተቃውሞን ደግሞ በበረገጉና በባተቱ ቁጥር ንጹሓን ዜጎችን ቁምስቅላቸውን በማሣየት በእኔን ያዬህ ተቀጣ አፍን ማዘጋት ነው፡፡ ለነገሩ በነሱ አይፈረድም፡፡ አያድርስ ነው ማለት፡፡ በታሪክ ዕብደትና ቅብጠት የተነሣ እነዚህ ሰዎች ለዚህ ገነት መሣይ ሲዖል አንዴውኑ ተዳርገዋል፡፡ የማርያም በር ደግሞ አይፈልጉም፤ እንደመጽሐፉ ቃል ልባቸው ወደ ድንጋይነት ተለውጧልና ምናልባት ሲወድቁ እንጂ ከመውደቃቸው በፊት ጊዜና አስተዋይ ልቦና አግኝተው ቆም ብለው የሚያስቡ አይመስለኝም፡፡ ሁኔታው ያሳዝናል፤ እነሱም ያሳዝናሉ፡፡ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብም ለመሪነት ቀርቶ ለተመሪነትም በማይመጥኑ በነዚህ ድንጋዮች ከሁለት አሠርት ዓመታት በላይ እንደሰም ቀልጦ እንደብረትም ተቀጥቅጦ መገዛቱ የሚገርም ክስተት ነው፡፡ ሲያስቡት ውለው ሲያስቡት ቢያድሩ የዚህ ታሪካዊ ቀመር ለማንም የሚከሰትለት አይመስለኝም፡፡ ቧልታይ ድንቃይ የሚመስል ግን የሚመርና የሚዘገንን ኤዞፓዊ ቀልድ ነው፡፡ኢትዮጵያን የመሰለች የድንቅ ታሪክ ባለቤት በነዚህ “ልጆቿ” እጅ ስትወድቅ ይታያችሁ፡፡ እነአክሊሉ ሀ/ወልድና እነራስ አሉላ በወጡበት ማኅጸን እነልደቱ አያሌውና መለስ ዜናዊ ሲወጡበት ይታያችሁ፡፡  ለዚቅ ያህል “የቆዬ ሰው ከሚስቱ ይወልዳል” ማለት አሁን ነው፡፡ “ዘመነ ግርምቢጥ ውሻ ወደግጦሽ፣ አህያ ወደሊጥ” – ነፍስ ይማር ገሞራው፡፡

በገደምዳሜም ቢሆን ለማለት የፈለግሁትን ሳትረዱልኝ የምትቀሩ አይመስለኝም፡፡ ማለት የፈለግሁት ባጭሩ “ወያኔዎችና ኢስላሚክ ካሊፌቶች የሚባሉት የአንድ ሣንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው” ነው፡፡ ቁጭ ብለው የሰቀሉት ቆሞ ማውረድ እያቃተ ኢትዮጵያም ሆነች የተቀረው ዓለም በጥቂት ሽፍቶችና ወሮበሎች እየታመሰ የመገኘቱ ዕንቆቅልሽ አስገራሚ ሆኗል፡፡ ወያኔዎች ከአሥራ አንድ ዘልለው ያልጠገቡ ጮርቃ ሕጻናትና ከአምስት ጥግንግን ጠበንጃዎች ተነስተው ይሄውና በሀገራችን ታሪክ ላይ መቼም ሊፋቅ የማይችል ጥቁር ጠባሳ አሣርፈው ወደማይቀርላቸው የታሪክ መዝገብ ሊሠተሩ ጫፍ ላይ ደርሰዋል – እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ፡፡ በዬዓለም ማዕዘናቱ የፕላኔታችን ራስ ምታት የሆኑ ቁጥር ሥፍር የሌላቸው አሸባሪ ቡድኖችም ለዚህ ወይ ለዚያ ድብቅ ዓላማ ማስፈጸሚያ ሲባል በተወሰኑ የዓለም ኃያላን መንግሥታት ወይም በኅቡዓን የመንግሥታት ተቆጣጣሪዎች (cabals) አማካይነት ይፈጠሩና በወርድና ቁመት – እንደዝንጀሮ ልጅ ማለት ነው – ጠንከር የማለት ስሜት ሲሰማቸው ከተሠሩበት ዓላማ ይወጡና ፈጣሪዎቻቸውን ሣይቀር ክፉኛ መገዳደር ይጀምራሉ፡፡ በዕንቁላሉ ያልተቀጣ ልጅ ደግሞ አንዴ መረን ከለቀቀ በኋላ መመለስ እንደማይቻል ከኛ በላይ አዋቂ ሊኖር አይችልም፤ በመጨረሻው ከባድ የሕይወት ዋጋ ክፍያ ተምረነዋል፡፡ ከህዋስ ደረጃቸው በመውጣት ከጎሬያቸው አፈትልከው በአሁኑ ወቅት ዓለምን እያመሱ ያሉት ወያኔን መሰል የሥውር ድርጅቶቹ ተላላኪዎች ጊዜያቸውን በደንብ እየተጠቀሙበት ይመስላል፡፡ ጊዜ ወሳኝ ነው፡፡ ነገ የነሱ እንደማትሆን ትናንት የነሱ ያልነበረ መሆኑን በማስታወስ የሚረዱት ሃቅ ነውና በጊዜያቸው ያሻቸውን ያደርጋሉ፡፡

የኞቹ በዘግናኝ ጭካኔያቸው ሀገራዊ ፍርሀትን አንግሠው 90 ሚሊዮን ሕዝብ ፀጥ ረጭ ሲያደርጉ እነዚያኞቹ ደግሞ የጋዜጠኞችንና የረድኤት ሠራተኞችን አንገት እየቀነጠሱ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ በፍርሀት ማራድ ነው – በፍርሀት የማራድ አዲስ ፖለቲካ፡፡ መድሓኒቱ እርግጥ ነው  አለመፍራት ነው፡፡ ግን እንዴት ይቻላል? ፍርሀትን ማስወገድ ትልቁ የሰው ልጅ ተግዳሮት ይመስለኛል፡፡ አለመፍራት ብቻም አይደለም የኞችን በተመለከተ ልዩነቶችን አስወግዶ እጅ ለእጅ በመያያዝ በኅብረት ታግሎ የነዚህን አይሲሊስት ወያኔዎች አደጋ ማስወገድም ቀላል ነበረ፡፡ አሁንም ቢሆን ዘዴያቸውን መረዳትና ከናካቴው ለይቶልን ሳንጠፋ መንቃት ይገባል ፡፡ ግን እንዴት እንንቃ? አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው የምንገኘው፡፡ ንቃቃት በመፍጠር የተካኑ ናቸው፤ ሌላ ችሎታ የሌላቸው እስኪመስሉ ድረስ በተቃዋሚዎቻቸው መካከል ልዩነትን መፍጠርና እርስ በርስ ማባላት ልዩ ችሎታቸው ነው፡፡ ጤናማ ሰው ተኝቶ ያድራል፡፡ እነሱ ግን ተንኮል ሲጎነጉኑና ሸር ሲጠነስሱ ስለሚያድሩ በዐይናቸው እንቅልፍ የሚዞር አይመስልም፤ ካባሊስቶች በተፈጥሯቸው አደገኞች ናቸው፡፡ በቁጥር አናሳነታቸው በሚፈጥርባቸው ልዩ ሥነ ልቦናዊ ጫና ምክንያት በፍርሀት ተውጠው ስለሚኖሩ የገዛ ጥላቸውን ሣይቀር ይጠራጠሩታል፡፡ ፍርሀት መጥፎ በሽታ ነው፡፡ ከነተረቱ የፈሪ ዱላ ዘጠኝ ነው ይባላል፡፡ የጀግና ግን አንድ ነው – ያንንም አዘውትሮ አይጠቀምበትም – እውነተኛ ጀግና ታጋሽና ይቅር ባይ ሊሆን ይገባዋልና፡፡ የፈሪ ዱላ ግን አያድርስ ነው – መቆሚያ መቀመጫ ነው የሚያሣጣ – ልክ አንድን በሬ ያሸነፈች በለስ የቀናት ላም ዓይነት፡፡ ወያኔን መሰል ካባሊስቶች ሁል ጊዜ በፍርሀትና በድንጋጤ ውስጥ ተሸብበው ስለሚኖሩ ሁሉንም ነገር ወደሥጋት የመለወጥ ባሕርያቸው የጎላ ነው፡፡ በዚያም ምክንያት ዱላ ከእጃቸው አይለይም፤ ያገኙትንና ከነሱ የተለዬ የሚመስላቸውን አለርህራሄ ይዠልጡታል፡፡ ሕይወታቸው እንደዚህ የተመሰቃቀለ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት የሰቀቀን ኑሮ ደግሞ ባፍንጫ ይውጣ የሚባል ነው፡፡ አሁን ወያኔዎች ከሥልጣን ሲወርዱ ሃያ አራት ዓመት እንደገዙ ሊነገርላቸው ይሆናል – ሀገር ተገዝቶ ተሙቶ፡፡ ድንቄም፡፡ ዜጎችን ማጋጨትና ማናጨት፣ ዕረፍት በሌለው ሁኔታ ሀገርን ሲሸጡና ሲለውጡ መባዠት፣ በማን መጣብኝ የሠርክ ድንጋጤ በመባነን ሌት ተቀን መቃዠት … ሀገርን እንደማስተዳደር የሚቆጠር ከሆነ – እውነት ነው – ወያኔ ኢትዮጵያን 24 ዓመታትን ገዝቷል፡፡ ያቆየንና ታሪክን ለማንበብ ያብቃን፡፡

ቦኮ ሃራም፣ አልቃኢዳ፣ ታሊባን፣ አልሻባብ፣ አይስል፣ ሎርድስ ሬዚስታንስ፣ ሕወሓት፣ ወዘተ. አንድ ናቸው ብለናል፡፡ አንድ ሰው በጥይትም ገደልከው በጩቤም አረድከው ውጤቱ ያው ነፍስን ከሥጋ መለየት እስከሆነ ድረስ ለኔ ብዙም ለውጥ የለውም፡፡ አፅንዖት ልሰጠው የሚገባኝ አንድ ነገር ደግሞ አለ፡- ሕወሓት እንዲያውም አይስልን በዋናነት ጨምሮ ከሌሎች አሸባሪዎች በተለዬ መልኩ የባሰ አረመኔ ነው – በዚያ ላይ መንግሥታዊ ዕውቅናና መንግሥታዊ ተቋምነት ተደርቦበት እንግዲህ የጭካኔው ልክ ይታያችሁ፡፡ የወያኔን ዓለም አቀፍ ምስልና የወዳጆቹን ቅባት(ሬቶሪክ) ተውት – የዐይጥ ምሥክር ድምቢጥ ነውና፡፡ እናም የጭካኔያቸውን ደረጃ ስናይ በግልጽ እንደሚስተዋለው ሌሎቹ በመግደል እንጂ በማሰቃየት የወያኔን ያህል አይደሰቱም ባይ ነኝ – የንጽጽር ጉዳይ ነው – የሎጂክም፡፡ ሕወሓት ግን የሚጠላውን መግደል ብቻ ሣይሆን ከመግደሉ በፊትና በኋላም ማሰቃየቱና ማንገላታቱ እጅግ ያስደስተዋል – ሬሣን በማንገላታት የምትደሰት እኔ እስከማውቀው ድረስ ድመት ብቻ ትመስለኝ ነበር፡፡ ይህ የወያኔ ‹ሳዲስት› ጠባይ ተብሎ ተብሎ ያለቀ ጉዳይ ነው፡፡ ሳስበው ከነሱ ጋር ተደምረን ዘጠና ሚሊዮን መባላችን በጣም ያንገበግበኛል፡፡ ከሰው ጋር ብቆጠር ያለ ነው፤ እንዴት ከዐውሬ ጋር እደመራለሁ?

በመሠረቱ ጭካኔ ዱሮም ነበር፤ አሁንም አለ፡፡ ደረጃው ግን እስከዚህን ድረስ ሲለያይ የሰውን ልጅ የሰው ልጅነት እንድንጠራጠር ያስገድደናል፡፡ ልብ በል፣ አንድን በወንጀል የሚጠረጠርንም ይሁን ንጹሕን ዜጋ ብርሃን የማይታይበት ጉድጓድ ውስጥ ጥለህ በዘር ጥላቻ የተመረዘ አጸያፊ ስድብ እየሰደብከውና እየደበደብከው፣ እየረገጥከውና ምራቅህን እየተፋህበት – ድምጽ እንዳያሰማ፣ እንዳይገላበጥ፣ ሰውነቱን እንዳያክ፣ እንዲራብና እንዲጠማ … አድርገህ አበስብሰህ መግደል ምን ማለት ነው? የየትኛው ሰማይ ወይም የየትኛው ፕላኔትስ ህግ ነው? የየትኛውስ ሃይማኖት ቀኖናና ቃለ ዐዋዲ ይሆን? የእነዚህ ሕወሓቶች ጭካኔ ታዲያ ከማንኛውም ምድራዊ አረመኔ ተግባርም ሆነ ከጋራ አባታቸው ከሰይጣን ጭካኔ አይበልጥምን? ማሰርስ ቢፈልጉ ለምን በአግባቡ አያስሩም? መግደልስ ቢፈልጉ ለምን በአግባቡና በክብር አይገድሉም? እነሱስ ከሰው አልተፈጠሩምን? ሰብኣዊ  ኅሊናቸውን እስከዚህን አሳዛኝ ደረጃ ያሣወረውን የአረመኔነት ባሕርይ ከየት ወረሱት እንበል? ዘወትርና ከጥንት በረሃ ሳሉ ጀምሮ የሚያስጨንቀኝ ይህ ጥያቄ ነው፡፡ ጭካኔያቸው እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው ማንና እንዴትስ ቢበድላቸው ይሆን? ተበድለውስ ቢሆን በደል በይቅር ባይነትና በሆደ ሰፊነት እንጂ በሚከፋ በደል ይመለሳል ወይ? ዐመፅ ዐመፅን እንደሚወልድ እንዴት ዘነጉት? ተበድያለሁ ብሎ በረሃ የገባና የታገለ ሰው እንዴት መፈጠርን የሚያስረግም ግፍና በደል የገዛ ወገኑ መሆኑን አምኖ ሊቀበለውና ሊንከባከበውም በሚገባ ሰብኣዊ ፍጡር ላይ ይፈጽማል? ለዕርቅና ለግልግል በሚያስቸግር መልኩ ለምን ይህን ያህል ጨከኑ? ምሥጢሩን የምታውቁ አካፍሉን፡፡ ብርቱ ጸሎት ግን ያስፈልገናል! የገባ ገብቶብናል፡፡ አንዲትን ነፍሰ ጡር የፈለግኸውን ያህል ብትጠላት እንዴት ሆዷን ረግጠህ ለስቃይና ለውርጃ ትዳርጋታለህ? እነሱስ በዚያ ማኅጸን አይደለምን የወጡት? ሰይጣን ራሱም እንዲህ ያለ ነውር የሚፈጽም አይመስለኝም፡፡መጥፎ ድርጊት ዳር ድንበር ሊኖረው ይገባል፡፡ በወጣትነት ዘመኔ ያየሁት “The Evil that Men Do”የሚል ፊልም ነበር፡፡ የነዚህ ከዚያም የከፋ ነው፡፡ ወደር የሚገኝላቸው አይመስለኝም፡፡ እግዚአብሔር ምሕረቱን ይላክላቸው፡፡ በጽኑ ታመዋልና፡፡ …

 

ይታየኛል፡፡ ደግሞም በገሃድ የሚታየውን እውነት በግልጽ በመናገሬ አሟረትህ አትበሉኝ ወይም እንዳትሉኝ፡፡ እንደገና ደግሞም ዱሮ ብዙ ነገሮችን ለፍልፌ ሳበቃ ከሞላ ጎደል አንዱም ተግባራዊ ሣይሆን አለመቅረቱን አስታውሱልኝ – ምላሴ ጥቁር ነው ማለት አልፈልግም፤ ባይሆን በወደድኩ እንጂ ልበል፡፡

በስደት ከምኖርበት ሀገር ሆኜ ስለሀገሬ እንደምሰማው ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተንተከተከ ያለው ድፍድፍ መፈንጃው ተቃርቧል፡፡ ይህ ሕወሓት የዘለለው ጠላ ምርጊቱን ፈንቅሎ ወይም ጋኑን ሰብሮ ሊወጣ የቀረው ጊዜ በጣም ኢምንት ነው፡፡ ሰኞን አለመሆን እንጂ ከሆኑ በኋላ መቆጨት ትርፍ የለውም፡፡ ትልቅ ሰው በሀገር ውስጥ የለም፡፡ ሜሮን ጌትነት በግጥሟ እንደጠቆመችው ዋርካዎች ተቆራርጠዋል፤ ሰንሰልና ሣማ ብቻ ነው እዚያና እዚህ ጉች ጉች ብሎ አገር ምድሩን አጥለቅልቆት የሚገኝ፡፡ ምራቅ የዋጡ አስታራቂ ሽማግሌዎችንና ተደማጭ ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ስብዕናዎችን ወያኔዎች በሥልት ጨርሰዋቸዋል፤ ከየዘሩ እየለቀሙ በአነር አስበልተዋቸዋል፡፡ ጥቂት እርሾ ቢኖሩም እንኳን በፍርሀት ተሸማቀው – በዘራቸው ማንነት ወይም በሌላ ምክንያት አንገታቸውን ደፍተው – የዕለት ተለት ሕይወታቸውን እንደምንም ከመምራት ባሻገር የሚፈይዱት ነገር እንዳይኖር ተደርገው ተሸመድምደዋልና አንድ ነገር ቢነሣ የሚያስታርቅ ተሰሚ ሰው አለን ማለት ይቸግረኛል፡፡ ሀብትም ሆነ ዝናና ክብር የምታገኘው ከወያኔ ጋር ስትሞዳሞድና መስህ ስታጨበጭብ በመሆኑ ከነሱ ጋር ያልተጎናበሰ የኅሊናው ሰው ለማግኘት በቀላሉ አትችልም – ታዋቂ ስፖርተኛም ሁን ነጋዴ ወይም የአርት ሰው በቀጥታም ይሁን በተዛዋሪ መርፌያቸውን ይወጉህና ከራስህም ከሀገርህም ከሕዝብህም ሣትሆን ከሁሉም ጋር ዐይንና ናጫ እንድትሆንና እንትን የነካው እንጨት ሆነህ እንድትቀር ያደርጉሃል፡፡ ‹ሳዲስቶቹ›(ሀዘን አምላኪዎች?) የሚያነካኩህ  ብዙ ዘዴ አላቸው፡፡ ለአብነት ያህልም የሚዲያ ሽፋን ለማግኘት ስትል የነሱን ቱሪናፋ በመናጆነት የምታናፍስበት ሁኔታ አለ – ለጉዳይህ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ብትከራያቸው፡፡ ወያኔ ብዙ ሰው አሳጥቶናል – ተፈጥሯዊ የተለዋዋጭነትና የአሽቃባጭነት ባሕርይ ሲጨመርበት ደግሞ ነገሩ ይከፋል – እንጂ ገነት ዘውዴና ሙሉጌታ አሥራተ ካሣ፣ ዳዊት ዮሐንስና አሰፋ ብሩ፣ ክፍሌ ወዳጆና ብርሃ ዳምጤ ጭንቅላት በሰም ካስት ይደረግ ይመስል በየጊዜው እየተለዋወጡ ከሰውነት ተራ ባልወጡ ነበር፡፡

ለማንኛውም የምንፈራው ነገር – ‹ቢቀሰቀስ› የሚል ባዶ ተስፋ እንኳን የለኝም – ለጊዜው ባለኝ ግንዛቤ  ‹ሲቀሰቀስ› ነው ማለት የምፈልገው – እናም የሚፈራው ማኅበራዊ ቀውስ ሲቀሰቀስ ለዘር የሚተርፍ ሰው የሚኖር አይመስለኝም፡፡ ከራስ በላይ ንፋስ ብሎ ሀገራችንን ለማፈራረስ ቆርጦ የተነሣው ሕወሓትና የውጭ ስፖንሰሮቹ የዘረጉት ወያኔዊ አጥፍቶ የመጥፋት ሤራ የያዘላቸው ይመስላል፡፡ በ40 ዓመታት ሊበርድላቸው ያልቻለው የቂምና የጥላቻ ቋጠሮ እየባሰባቸው ሄዶ አሁን አሁን ከናካቴው እንዳበደ ውሻ የሚሠሩትን አጥተው ዕልቂትን እየጋበዙ ይገኛሉ፡፡ ትዕቢትና ዕብሪታቸው ለከት አጥቶ ዜጎችን ከጉንዳንና ከዝምብ ባለፈ እንደሰው መቁጠር አልፈለጉም፡፡ እንደተወለዱ ያረጁት እነዚህ ወያኔዎች የሀገራዊ ማንነት ስሜትም ሆነ ሰብኣዊነት ስለሌላቸው ምንም ነገር ቢፈነዳ ጉዳያቸው አይመስልም፡፡ ዓላማቸውና የመጨረሻ ዕቅዳቸው ሀገሪቱን የደም አላባ ውስጥ ዘፍቆ ወደሚቃዡባት የተስፋዋ ምድር ትግራይ-ትግሪኝ ለመንጎድ ያቆበቆቡ ይመስላሉ – እዚህ የሚፈነዳው ሽንት ቤት ጎረቤት ድረስ ሽታው ተዛምቶ መላ አካባቢውን እንደማይበክል በምን እንዳረጋገጡ አላውቅም፡፡ የዕውቀት ድሆች ስለሆኑ ከየሚያስቡት ዕውር ድምብራዊ ቅዠት በስተኋላ ሊከሰት የሚችለውን መለኮታዊም በሉት ሰብኣዊ የአጸፋ ድርጊት ሊያስቡ አይችሉም ወይም አይፈልጉም፤ ምክንያቱም በድፍን ቅልነት ሊመሰል የሚችል ባዶ ጭንቅላታቸው በጥጋብና በዕብሪት ተወጥሯልና፡፡ ዕውቀታቸው – ዕውቀት ከተባለ – መብላት፣ መጠጣትና መራባት የሚያስችል እንስሳዊ የደመ ነፍስ ዕውቀት ነው – ከተንኮል በተጓዳኝ፡፡ ለነገሩ ከእረኝነት ተነስቶ ጄኔራል ከሆነ ሰው ብዙም የሚጠበቅ ነገር የለም – ብቻ አልታደልንም፡፡ ትዕቢትና ዕብሪት ደግሞ ወደ ውድቀት እንደሚመሩ በፍጹም አያውቁም፤ ከታሪክም መማር ዕርማቸው ነው – ለነሱ ታሪክ ማለት ጠግቦ ማደር ነው፡፡ ወያኔ ከእግዜሩም በላይ ነው – ይህንንም “እንኳንስ ከአመሪካ ከመንግሥተ ሰማይም እናስመጣሃለን!” ሲል አንዱ ጥጋበኛ ወያኔ ለሰሎሞን ክፍሌ በግልጽ ባስተላለፈው ዛቻ መረዳት ይቻላል – ድፍን ቅልነት ከዚህ በላይ የለም፡፡ መታወቅ ያለበት ነገር ታዲያ በትምክህት የታወረ ስብዕና መጨረሻው ዕልቂት ብቻ መሆኑ ነው፡፡ ችግሩ ደግሞ ሟች ይዞ ይሞታልና ለጠገበ የሚላክ መቅሰፍት የተራበንም መጨመሩ ነው፡፡

ስለዚህ ውድ ወገኖቼ!

ለሀገራችሁ ነፃነት ስትሉ በበረሃና በዱር በገደል የምትንከራተቱና የምትዋደቁ [ካላችሁ] እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን፡፡ በበርካታ ቡድኖች ተበጣጥቆ ይህን የኢትዮጵያ ኢስላሚክ ካሊፌት(አጠራሬ ሃይማኖታዊ አንድምታ እንዳይዝብኝ) አሸንፋለሁ ማለት ፍጹም ዘበት ነው፡፡ ስለዚህ ምንም ነገር ከመጀመራችሁ በፊት ኅብረትና ውህደት ፍጠሩ፤ በሌለች ሀገርና በሌለ ሥልጣን በባዶ መሬት አትወዛገቡ፣ አትጨራረሱም፡፡ ሥልጣኑን ከሕዝብ ለመቀበል በቀናነት ትጉ እንጂ መሠሪ ተንኮል በልባችሁ አሸምቃችሁ ወደ ትግል አትግቡ – መጨረሻው ኪሣራ ነውና፡፡ ከወያኔና ከደርግ ብዙ መማር ይቻላል፡፡ “የሞኝ እንትን ካለአንድ ቀን አይበልጥ” እያለ በሥነ ቃሉ በሚተርት ሕዝብ መሀል የልብን መሥራት በመጨረሻው ወደ ጥልቅ እንጦርጦስ እንዴት እንደሚከት ከዐፄው ጀምራችሁ በተከታታይ የመጡትን የበረከተ-እርግማን ተጋሪዎች ዕጣ ፋንታ በማጠየን መረዳት ይገባችኋል፡፡ ስለሆነም በአንድ የዕዝ ሰንሰለት ውስጥ ገብታችሁ በጋራ የጋራ ሀገር ባለቤት የምትሆኑበትን ሁኔታ አሁኑኑ አመቻቹ እንጂ በየጎጡ መሽጌ ዘመነ መሣፍንትን እደግማለሁ ብትሉ ሕዝ ነቅቷልና አንቅሮ ይተፋችኋል፤ የሕዝን የልብ ትርታ አድምጡ – ለምሣሌ ዴምሃት የሚባለው ድርጅት በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ መዋቡ ግሩም ሆኖ መሀሉ ላይ የአክሱምን ሀውልት ማኖሩ ተገቢ አይመስለኝም፤ እንደግል ተቋም ዓርማነት ከሆነ አላውቅም፡፡

አሁን ጊዜ የላችሁም፡፡ ተጨማሪ ደቂቃ ባጠፋችሁ ቁጥር አይስሎቹ በሤራ ጉንጎና ቀላል ስላልሆኑ እየጠነከሩ ይሄዳሉ – ከጎናቸው የተሠለፉ ኃይሎችም ቀላል አይደሉም – ፈጣሪ ለራሳቸው የቤት ሥራ ካልሰጠልን በቀላሉ የሚተውን አይደሉም፤ ኢትዮጵያዊነት ልዩ ብሔራዊ ኩራት የዓለምን ሰላም የሚያደፈርስ ይመስል እንደወገብ ቅማ ጠምደው ከያዙን ብዙ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ለነሱ አደግዳጊ ያልሆነ መንግሥት አይፈልጉም – በየሀገራቱ ይህን የማስገበር ሥርዓት ይተክላሉ – እምቢ የሚልን ይገድላሉ/ያስገድላሉ፡፡ ስለሆነም ከዚህ ነጥብ አንጻር ተጠንቀቁ! ሕወሓቶች መቼም ቢሆን ብቻቸውን ሆነው ለድል በቅተው አያውቁም፡፡ የኢትዮጵያ እንደሀገር በራሷ እግር መሄድ እንደ እግር እሳት የሚያንገበግባቸው ከሩቅም ከቅርብም ብዙዎች አሉና ትግላችን መራራ መሆኑን ተገነዘቡ፡፡ ወያኔ ሞተ ሲባል እንደባብ አፈር እየላሰ የሚነሳበት ምክንያት ሌላ ሣይሆን ይኼው መርዘኛ ጭራውን ከነዚህ የሀገራችን መሠሪ ጠላቶች ጋር በማስተሳሰሩ ነው፤ የከንፈር ሽንገላውንና የዐዞ ዕንባውን ብዙም አትመኑት – የአዛኝ ቅቤ አንጓችነት ከጥንትም ነበርና እውን በማይሆን ከንቱ ተስፋ አትደለሉ፡፡ ፈጣሪያችን ትቶ አይተወንምና እናንተ ተስማምታችሁ ቀጥሉ፡፡ ስምምነት ከሌላችሁ ግን ፈጣሪ ከእናንተ ጋር አያብርም፤ ፈጣሪ ከሁለት ዕኩያን ለአንዱ አያዳላም፤ ንጹሕ ልብስን ለብሶ በቆሻሻ ቱቦ ውስጥ ማን ሊያልፍ ይሞክራል? ስለዚህ የርሱን ድጋፍ ለማግኘት ከወያኔ የተሻለ የጠራ ስብዕናና ሕዝባዊ ወገንተኝነት ሊኖራችሁ ይገባል እላለሁ፡፡ ደግሞም ለለውጥ መነሣታችሁን ከራሳችሁም በበለጠ ፈጣሪን ለማሳመን ሞክሩ፤ ያኔ በርግጠኝነት ይረዳችኋል፡፡ የፈጣሪ እገዛ የሌለበት የነፃነት ትግል ፍሬው ለሕዝብ አይደርስም – እጫፍ ይቀራል፡፡ እነመለስ ዜናዊ ትግላቸው ለራሳቸው እንጂ ለሕዝብ አልነበረም፡፡ ፈጣሪን የማያውቅ ሕዝብን አያውቅም፡፡ እንዴት ተድርጎ?

ሀገርና ሕዝብ ሲባል ደግሞ በየዘፈኑ እንደምንሰማው ወንዝና ሸንተረሩ አይደለም፡፡ እሱ እሱ ነገር ለማሳመርና ተቀባይነትን ለማግኘት እንጂ ሀገር ማለት የመሬት ቅርጽና የውኃ አካላት ማለት ሣይሆን ሕዝቧ ማለት ነው፡፡ እናም ሕዝቡን ውደዱት፡፡ ይህን በተተካኪ መንግሥታዊ ዱላዎች እየተቀጠቀጠ ያለ ሕዝብ ከልብ አፍቅሩት፡፡ የእያንዳንዱ ዜጋ ዕንባና ሰቆቃ የእያንዳንዳችን እንደሆነ ያህል ካልተሰማን የነፃነት ታጋይ ልንሆን አንችልም፡፡ የክርስትና ሃይማኖት የማዕዘን ራስ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ “የሚወደኝ ቢኖር መስቀሌን ተሸክሞ ይከተለኝ” እንዳለው የሕዝቡን መከራና ስቃይ እንደራሳችን ቆጥረን ጎንበስ ብለን ዕንባውን እናብስለት፡፡ ከማስመሰልና ከታይታ ተቆጥበን ቅድመ ሁኔታ በሌለው ፍቅር ሁላችን እንተሳሰር፤ የነፃነት ታጋዮች የሆናችሁ ሁሉ እርስ በርሳችሁም ተሳሰሩ፡፡ ያኔ ሕዝቡም ከአንጀት ይወዳችኋል፡፡ የምሬን ነው – አንዳችን ለአንዳችን ልባዊ ፍቅር ይኑረን፤ ለበጣና ማስመሰል ቅር፡፡ በሀብት፣ በገንዘብ፣ በትምህርት፣ በዕድሜ፣ በሃይማኖት፣ በዘውግ፣ በጤንነት ፣ በፆታ፣ በመልክና በቁመት … ልንለያይ እንችላለን፤ ተፈጥሯዊም ነው፡፡ ግን ሁላችንም ሰዎች ነን፡፡ ቢቻል በሰውነታችን ያ ቢከብደን ደግሞ ቢያንስ በአንዲት ሀገር የጋራ ባለቤትነታችን እርስ በርስ እንዋደድ፡፡ የማያውቀን ፈረንጅ ልብሱን ከገላው እያወለቀ፣ ምግቡን ከጉሮሮው እየነጠቀ እኛን በዘር በቀለም የማንገናኘውን የዓለም ዜጎች በሰብኣዊነት ሲረዳን እኛ የአንዲት ሀገር ዜጎች ካለበቂ ምክንያት የምንነካከስበትና ጀርባ የምንዟዟርበት ሁኔታ ሊኖር ፈጽሞ አይገባም፡፡ ቂምና ጥላቻን ከማስወገዱ በተጓዳኝ ያለን ለሌለን እንርዳ፡፡ ስንፋቀር አንዱ የሁሉም፣ ሁሉም የአንዱ ይሆናል፡፡ ስንፋቀር ተዝቆ የማያልቅ በረከት(ረድኤት ማለቴ ነው) ይኖረናል፡፡ ስንፋቀር አንጨካከንም፤ ፍቅር ሁሉንም የክፋት ምንጭ የሚያደርቅ ከእውነተኛው ፈጣሪ የምትገኝ መለኮታዊ ማርከሻ ናት፡፡ በምንፋቀር ጊዜ ለመገዳደል የሚሮጡ እግሮችና ለመቦጫጨቅ የሚያሰፈስፉ እጆች ለመረዳዳትና ለመጎራረስ ይሽቀዳደማሉ፡፡ ያኔ ሰይጣንን ቀንዱን መትተን  አሸነፍነው ማለት ነው፡፡ ሰይጣን መሸነፉን ሲያውቅ ተስፋ ቆርጦ ይተወናል፡፡ ያኔ ለኛ ቀርቶ ለሌላ የሚተርፍ ሀብት ወይም እርዚቅ ይኖረናል፤ ልብ ባንል ወይም ልብ  ብንልም ዕድሉን ስላጣነው እንጂ እኛ ኢትዮጵያውያን ከእግራችን ሥር ወርቅና አልማዝ ቀብረን እላዩ ላይ ቆመን የምንቧቀስና በማን አባት ገደል ገባ የጠላቶቻችን መስተፃልዓዊ ድግምት የምንገዳደል ምሥኪን ፍጡራን ነን፤ ስንቧቀስም እየተዋጋንና ዕየተራብን በሁለት መንገድ እናልቃለን – በጦርነቱና በርሀቡ፡፡ በማከያው ግን ለጥቂት መሠሪዎች የሀብት መቆናጠጫ እንደሆን እንኖራለን – እሞኝ ደጃፍ  ሁሌም ሞፈር እንደተቆረጠ የዓለም ፍጻሜ ተቃረበ! ጥያቄው “በዚሁ እንቀጥል ወይንስ ካለፈው ተምረን አስተሳሰባችንን በማዘመን እንሻሻል?” የሚል ነው፡፡ ልብ እንበል – ፍቅር በሌለበት የገበታ ማዕድ ባዶ ነው፡፡ ባዶ ማዕድ ይዘህ ደግሞ ስደትንና በተንኮል መጠማመድን፣ መመቀኛኘትንና መፋጀትንም አታቆምም፡፡ ስለሆነም ታጋዮች በአዲስ መንፈስ ታግላችሁ አታግሉን፡፡  ተመሳሳይ አረንቋ ውስጥ ደግመን እንዳንዘፈቅ ትታደጉን ዘንድ ኅሊናዊና መንፈሣዊ ዕድገታችሁ እንደወያኔዎቹ ቀጭጮ እንዳይቀር ተግታችሁ ሥሩ፡፡ ሁሉም ነገር አላፊ ነው – ሀብትም ሥልጣንም ዝናም … በአንዴም ባይሆን በሂደት ይንኮታኮትና ሁሉም ነገር ወደነበረበት ይመለሳል – ወደባዶ፡፡ የማያልፈው ግን መጥፎና ደግ ታሪክ ነው፡፡ ምርጫው የራሳችን ነው፡፡ ደግ ታሪክ ሠርቶ በትውልድ መወደስ ወይም እንደነመንግሥቱ ኃ/ማርያምና መለስ ዜናዊ ዘግናኝ ታሪክ ሠርቶ በትውልድ መወቀስ፡፡

በዓለም ዙሪያ የተበተንን ኢትዮጵያውያንም ሆን በሀገር ውስጥ የምትገኙ ሁሉ፤

ኢራቅን፣ ሶማሊያን፣ አፍጋኒስታንን፣ ዩጎዝላቪያን፣ ሩዋንዳን፣ ሊቢያን፣ ሦሪያን፣ የመንን፣… የሚያስመሰግን አስከፊ ገጽታ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ኢትዮጵያ እየገሠገሠ ነው፡፡ ይህም የሆነው ጆሮ የሌለው የወያኔ ጉጅሌ ላለፉት ጥቂት የማይባሉ አሠርት ዓመታት ሕዝቡ ራሱና የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያውቁ ጠበብት የሚነግሩትን  (በቂም በቀልና ጥላቻ በመለከፉ ሣቢያ) በማወቅም ይሁን ባለማወቅ መስማት ባለመፈለጉ ይልቁንም ይህ አስከፊ ገጽታ እንዲከሰት ጠንክሮ በመሥራቱ ነው፡፡ ወያኔዎች ሀገራዊ ፍቅርና ስሜት ይቅርና ቅንጣት ሰብኣዊ ስሜት ቢኖራቸው ኖሮ ይህችን ሀገር ለማዳን ዋናው ቁልፍ በእጃቸው ነበር፡፡ ግን ተፈጥሮን ተመክሮ ስለማይመልሰው የዚህች ሀገር ዕጣ ፋንታ በፈጣሪና በጥቂት ቅን ልጆቿ መዳፍ ሥር ነው፡፡ ለሥልጣን ያሰፈሰፈው(አራት ኪሎ ያለችው አንዲት ወንበር ብቻ መሆኗን የዘነጉ ይመስላሉ) የግሪሣ መንጋ ጥቂት ባልሆበት፣ የዘረኝነት አዶ ከብሬ በጦዘበትና ያዙኝ ልቀቁኝ በሚልበት፣ ድህነቱና የኑሮ ውድነቱ ሰማየ ሰማያትን አልፎ የትዬለሌ በተወነጨፈበት፣ ሙስናው እግር አውጥቶ ከታች እስከላይ በተንሠራፋበት፣ አላግባብ ብልጽናው መረን ለቅቆ  ከዜሮ ሣንቲም ተነስቶ በቅጽበት ሚሊዮኔር በሚኮንበት፣ የነጋዴው ስግብግብነትና አለልክ ማትረፍ ቅጥ ባጣበት፣ ኤቢሲዲን በቅጡ ያልለየው ምድረ ማይም ዘረኛና አሽቃባጭ ባንዳ ሁላ ቢሮክራሲውንና የጦርና የፀጥታ ተቋማትን ባጥለቀለቀበት፣ አእምሮ ወደሆድ ወርዶ ሆድ ወደራስ ወጥቶ በተሰቀለበትና እነሆድ አምላኩ በነገሡበት … እጅግ አስጨናቂ ሁኔታ ላይ እንገኛለንና ሁላችንም ጊዜ ሰጥተን በጥሞና እንጸልይ፡፡ ችግራችን በጦር ብቻ እንደማይፈታ እንረዳ፡፡ ችግራችን በጩኸትና በጦር ቢፈታ ኖሮ ከ66 እና ከ83 ዓመተ ምሕረቶች አንድኛቸው በቂያችን ነበሩ፡፡ ስለዚህ የጎደለን ቅመም አለ ማለት ነው፡፡ እንደኔ ያ ጉድለት ጸሎት ነው – በነገራችን ላይ በምንም ዓይነት ፈጣሪ አለማመንን ወይም የተለያዬ እምነት መከተልን እንደማልቃወም ይታወቅልኝ፤ ሊከበር የሚገባው መብት ነው፤ (ኢ-አማኒ/ኤቲይስት ማለት ግን በኅሊናዊ የዕውቀት ሀብቱ የሚመራና ማኅበራዊ የአብሮነት ዕሤቶችን የሚያከብር ጥንቁቅ እንጂ እንደልቡ ፈንጣዥ ሊሆን እንደማይገባው አምናለሁ) ፡፡

በሀገር ቤት ቤተ ክርስቲያንና መስጂድ ለወያኔ ስላደሩ ጸሎት ማድረግ የሚቻል አይመስለኝም፤ ለወያኔ ባደረ ቤተ አምልኮ ተጸልዮ ደግሞ ጸሎቱ እንኳንስ ጽርሃ አርያምና መንበረ ፀባዖት ሊደርስ ከአፀደ ቤተ ክርስቲያን ጣሪያና ኮርኒስም አያልፍም፤ እኛ ልንቀልድ እንችላለን፡፡ ፈጣሪ ግን ለቀልድ ጊዜና ፍላጎት ያለው አይመስለኝም፡፡ እየተዋወቅን መተናነቁ ልትዝብት ይዳርጋል እንጂ አይጠቅምምም፡፡ በየምንኖርባቸው የስደት ሀገሮችም ሆነ በሀገር ቤት ካሉ  የቤተ አምልኮት አገልጋዮች ጋር አብረን እንውላለን፤ እናመሻለን፡፡ ጳጳሣትንና ሼሆችንም መንፈሣዊ ወሥጋዊ ድርጊቶቻቸውን እንከታተላለን፡፡ ያውቁናል – እናውቃቸውማለን፡፡ ለሥጋው ምቾት አድሮ የግፍ አገዛዝን ባለመቃወም ከዚያም ባለፈ ለጸረ-ሃይማኖቱ ዲያብሎሣዊ ኃይል መሣሪያ በመሆን ናቡከደነፆራዊው አገዛዝ እንዲቀጥል ማድረግ የነቅዱስ ጳውሎስንና የመጥምቁ ዮሐንስን ሰማዕትነት ማርከስ ነው፡፡ ወደ ዝርዝር ሳንገባ በነዚህ ዓይነት የሃይማኖት መሪዎች የሚድን ሀገርም ሆነ ሕዝብ እንደሌለ በመጠቆም ብቻ የሀገራችንን መራር እውነት ማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡ ስለዚህ በበኩሌ በዚያ በኩል ብዙም ተስፋ አላደርግም፡፡ እንደኔው በውጪ ያላችሁት ካህናትና ምዕመናን ይልቁናስ በርቱ – ከመሰል ሃሜታ ንጹሕ ከሆናችሁ፡፡(መጸለይ ያለበት ንጹሕ ሰው ብቻ ነው እያልኩ እንዳልሆነ ግን ይታወቅልኝ! በመሠረቱ ማንም ይሁን ማን ስህተትን መሳሳት ሰውኛ ነው – በስህተት ቆርቦ ስህተትን ባህል ማድረግ ግን እንኳንስ ከሃይማኖት መሪ ከተራ ምዕመንም አይጠበቅም… ኣ! ዝርዝር ኪስ ባይቀድ ኖሮ…፡፡)

በሀገር ቤት የቡድን ጸሎት በቤተ አምልኮዎች ካልተፈቀደ ሌላው አማራጭ በየግል በዓትና በቤትም ውስጥ ጸሎትን ማድረስ ነው፡፡ ያን የሚከለክል የለም፤ አይችሉምም፡፡ ግን ከልብ እንጸልይ፡፡ ስንጸልይ እንደልማዳዊው የአብዛኞቻችን ጸሎት “እመብርሃን፣ የእገሌን ነገር እስከዚህን ቀን ድረስ ካላሣየሽኝ ደጅሽን አልረግጥም!” ዓይነት ሣይሆን ከዚህ የተለዬ ሊሆን ይገባል፡፡ ከፍ ሲል በዘወርዋራ መንገድ ለመጠቆም እንደሞከርኩት ስንጸልይ ፈጣሪ እንዲሰማን የኛን ደጅ ቀድመን አጽድርተን መሆን አለበት፤ ፈጣሪ የሚሰማው ጸሎት ከንጹሕ ልብ፣ በንስሃ ከታጠበና ይቅርባይነትን ከተላበሰ ንጹሕ ሰውነት የሚወጣን እንጂ ከአስመሳይ አንደበት የሚንበለበልን ልፋፌ ጽድቅ እንዳልሆነ መረዳት ይገባል፤ ዋናው በጸሎቱ ውስጥ ያለው የቃላት ማማር ሣይሆን የልብ ንጽሕና ነው – የጸሎት ጎልዳፋ የለውም፡፡ ከእንስሳት ውስጥ እንኳን የሚጸልዩ እንዳሉ ይነገራል፡፡ ጸሎታችን ከልብ ከሆነና እንዴት እንደሚጸለይ ካወቅን፣ ምን መጠየቅ እንዳለብንና እንዴት መጠየቅ እንዳለብን ከተረዳን ፈጣሪ መልስ ለመስጠት ደቂቃ አይፈጅበትም፡፡ ጸሎትን ለማድረስም ሀገርን ከጫፍ እጫፍ ማካለል አይጠበቅብንም – መኝታ ቤትህ ሆነህ የሚሰማህ አምላክ ግሼንና አክሱም ጽዮን ተጉዘህ ባይሰማህ አትታዘበው( ሂድ/አትሂድ እያልኩ ሣይሆን ዋናውና ወሳኙ እግርህ ወይም አፍህ ሣይሆን ልብህ ነው እያልኩ ነው፤ ወንድሜ – የማታውቀውን እየነገርኩህ አይደለም – የተማርኩትን እያስታወስኩህ እንጂ)፡፡

በሌላም በኩል  ችግሩ የሚመስኝ የአጠያየቅ ጉዳይ  ነው፡፡ “ሄይ! ሰውዬ፣ አንድ ሺህ ብር የማትቦጭቅልኝ ምናባህ ቆርጦህ ነው!” ብለህ አንዱን ሀብታም ነጋዴ ብትለምነው – ይህ መለመን ነው እንዴ እሚባል ለነገሩ – ማለትም ብታፋጥጠው መስጠቱ ከባድ ላይንበት ቢችልም አጠያየቅህ ስለማያምር ግና ድምቡሎ የሚያቀምስህ አይመስለኝም፡፡ በዘበኛው ያባርርሃል ምናልባት፡፡ ስለጸሎት አደራረስም ብዙዎቻችን ጥቂት ማንበብ የሚኖርብን ይመስለኛል፡፡ ወይም አንዱ አንባቢ በራሱ ጊዜ ይመለስበትና ያስነብበን፡፡

ለማንኛውም ከሃያ ሦስት ዓመታት በኋላ – በደርግ መጨረሻ እንደመጣሁ – በወያኔም መጨረሻ ብቅ ብያለሁና በተለይ በዚያው የእሁድ ማለዳ የታምራት አሰፋ(ነ.ይ) ቆንጆ የንባብ አቀራረብ ትከታተሉኝ ለነበራችሁ ወገኖቼ  የናፍቆት ሰላምታየ በያላችሁበት ይድረሳችሁ(በተለይ የአዲስ ዘመኑ ወዳጄ እምሩ ወርቁ ባለህበት ሰላም ልበልህ)፡፡ እንደእግዚአብሔር ፈቃድ በስፋት የምንገናኝበት ዘመን መምጣቱ አይቀርም፡፡ ጸሎታችንን ሳናቋጥ ማድረሳችንን ግን አንርሣ፡፡ በየሃይማኖታችን እንጸልይ፡፡ ፍቅር ይኑረን እንጂ የሃይማኖት መለያየት በጭራሽ አያጣላንም – “አንቺም ባይማኖትሽ እኔም ባይማኖቴ” ብሏል ተወዳጁ አቀንቃኝ ቴዲ አፍሮ፡፡ የመተዛዘንና የመዋደድ በችግራችንም ጊዜ የመድረስ ቆንጆ ባህላችን እየደበዘዘ የመጣ ይመስለኛልና እንሰብበት፡፡ ከፍ ሲል ለማስታወስ እንደሞከርኩት ሀገርን ስናፈቅር መሬቱን [ብቻ] ሣይሆን ወገናችንን ዜጋውን መሆን አለበትና እንዲያው ለምሣሌ ሰው አንከላፍቶት ቢወድቅ “እኔን! ተጎዳህ? አይዞህ ወንድማለም/እህታለም” በማለት በሚያስፈልገውና አቅማችን በቻለ እንርዳው፤ እናጽናናውም – አየህ፣ አንተን እንደዚህ ቢሉህ ደስ አይልህም? አዎ፣ የቻይናውን ፈላስፋ የኮንፊሼስን ብሂል እንከተላት – “ሰዎች ባንተ ላይ እንዲያደርጉብህ የማትፈልገውን ነገር አንተም በነሱ ላይ አታደርግ”፡፡ ካልተረዳዳን፣ ካልተነፋፈቅን፣ እንደቀደመው ባህላችን በመዋደድና በመተሳሰብ አዳራሽ ካልተመላለስን የአንዲት ሀገር ዜጎች መሆናችን ጥቅሙ ታዲያ እምኑ ላይ ነው? የፈረንጆቹ ዘግቶ በላው “ባህል” ይቅርብን፡፡ ስንነግድም ተያይተን እንነግድ፡፡ ከአፍኣዊው ይልቅ ወደ ተግባራዊው የፍቅርና የመዋደድ መግለጫዎች በቶሎ እንዙር፡፡ እየጠፋን ስለሆነ ቆም ብለን እናስብ፡፡ የጥንቱን ፍቅርና መተሳሰብ እንዲመልስልን አላህን/እግዜርን በጸሎት እንጨቅጭቀው፡፡ እነዚህ የፍቅር መቀሶች ፈጣሪ እንዲገላግለንም ዘወትር በዱኣ እንነዝንዘው፡፡  የሰው እንጂ ሁለት የፈጣሪ ጆሮ ቁጥር ሥፍር የለውምና ይሰማናል – ከተለያየን ግን አይሰማንም፡፡ ደጋግሜ እንደምለው ሃይማኖትን የጠብ መንስኤ እንዳናደርግ እንጠንቀቅ፡፡ በማንም ሃይማኖት ማንም ጣልቃ አይግባ፡፡ የሚድነውንም ሆነ የሚጠፋውን የሚያውቅ አንድ ብቸኛ አካል ፈጣሪ ስለሆነ በመሰለን መንገድ ብናመልከው ተግባራችን መልካም እስከሆነ ድረስ በቀኖናና በመንገድ መለያየት ምክንያት ብንጣላ ግብዝነት ይመስለኛል፡፡ ጠበቃና ደም መላሽ የማያስፈልገው የፍጡራን ሁሉ ፈጣሪ ራሱ ስለራሱ ጥብቅና መቆም አያቅተውምና የማንም ሃይማኖት ተከታይ በማንም ሃይማኖት ጣልቃ ገብቶ ረቂቄን መንፈስና የሕይወት መፍለቂያ የሆነውን ኃያል ኑባሬ(Being) የሰውኛ ባሕርይ በማላበስ አቦካቶ ለመሆን አይዳዳ – በዚህን ዓይነቱ ቂልነት ፈጣሪ ራሱ ከትከት ብሎ ሣይስቅ የሚቀር አይመስለኝም፡፡ እሱ ስለራሱ ያውቅበታል፡፡ ይልቁንስ ስለራሳችን እንጨነቅ፤ ማንም እንሁን፣ ምንም ይኑረን ብዙ የሚያስጨንቁን ነገሮች ግን አሉ – የደስታና የሀዘን ምንጮች ደግሞ ገንዘብ ማግኘትና ማጣት ብቻ እንዳልሆኑ ሁሉም ያውቃል፡፡  መልካም የነፃነት ዘመን ያድርግልን፡፡እኔም ወደ ሀገሬ እንድገባ ጸልዩልኝ፡፡ ስደት ሰልችቶኛል፡፡ የሰው ሀገር ኑሮ ለተወሰነ ጊዜ እንጂ እስከወዲያኛው ሲሆን መፈጠርን ያስጠላል፡፡ ሰላም፡፡

 

ለማንኛውም ገምቢ አስተያየት፡- khartoum71@gmail.com

 

 

The post ሀገራዊ የጸሎት ጥሪ -ሰሎሞን ንጉሡ (ከሱዳን) appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2784

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>