ካለፈው ኦክቶበር ወር ጀምሮ ከመገናኛ ብዙኃንና ከሕዝብ እይታ የራቁት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጤንነት ጉዳይ እያነጋገረ ባለበት በዚህ ወቅት ፕሬዚዳንቱ በፖርት ሱዳን ዛሬ ታዩ።
እንደ ኤርትራ የማስታወቂያ ሚ/ር ድረ ገጽ ገለጻ ትናንት ከአስመራ ተጉዘው ወደ ፖርት ሱዳን የሄዱት ፕሬዚዳንት አፈወርቂ ወደዚያው ያመሩት በ7ኛው የቀይ ባህር የቱሪዚም እና የገበያ ፌስቲቫል ላይ ለመካፈል ነው።
የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከዓመት በፊት ሞተዋል ተብለው የተወራባቸው የነበረ ሲሆን “ለረዥም ሰዓት ተኝቼ ብነሳ በሶሻል ኔትወርኮች ሞተ ተባለ” ሲሉ በኤርትራ ቲቪ ላይ በወቅቱ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ተሳልቀው ነበር። ከሰሞኑም አቶ ኢሳያስ ከሚዲያ እና ከሕዝብ እይታ ከተሰወሩ ወር አለፋቸው በሚል ከፍተኛ የሚዲያ ማድመቂያ ወሬ ሆነው መሰንበታቸው የሚታወስ ሲሆን በፖርት ሱዳን የቀይ ባህር ቱሪዝም ፌስቲቫል ላይ ከአልበሽር ጋር መታየታቸው መዘገቡ ወሬውን ያቆመዋል ተብሏል።