Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » News
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2784

‹‹ዘጠነኛው ስቃይ›› – (እውነተኛ የወንጀል ታሪክ)

$
0
0

U.S. Immigration And Customs Officials Deport Undocumented El Salvadorians
በቀድሞው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሰው መግደል ወንጀል ምርመራ ክፍል ህንፃ ውስጥ በሚገኝ አንድ ደብዘዝ ያለ ብርሃን ያለው ክፍል ውስጥ ተቀምጧል፡፡ አሮጌ ጠረጴዛና ወንበር እንዲሁም ጥቂት ፋይሎች የተደረደሩበት የመጽሐፍ መደርደሪያ መሰል ነገር ጠበብ ያለውን ክፍል ለብቻቸው ይዘውታል፡፡

በተሰበረው የመስኮት መስተዋት በኩል ቀዝቃዛ አየር ይገባል፡፡ ታገሰ እና መርማሪ ፖሊሱ ፊት ለፊት ተፋጥጠዋል፡፡ በእንጨት ጠረጴዛው ላይ የተዘረጋው አረንጓዴ ቀለም ያለው የተከሳሽ ቃል መቀበያ ፎርም ላይ አቀርቅሮ የሚጽፈው መርማሪ ፖሊስ ታገሰ የሚናገረውን ነገር በሙሉ ይመዘግባል፡፡ አልፎ አልፎ ቀና እያለ ጥያቄ ይቀርብለታል፡፡

የተረበሸ ስሜቱ እያስታወቀበት ነገር ግን የተረጋጋ ለመምሰል እየሞከረ ቃላቱን በቀስታ ከአፉ እየጎተተ የሚያወጣቸው ታገሰ እዚህ ፖሊስ ጣቢያ የተገኘበትን ምክንያት ይተርካል፡፡ ይህ የ38 ዓመት ጎልማሳ በሰው መግደል ወንጀል ተጠርጥሮ ነው የተያዘው፡፡ የተጠረጠረበትን ወንጀል ደግሞ በራሱ የእምነት ቃል ትክክል መሆኑን አረጋግጧል፡፡ መርማሪ ፖሊሱ በወንጀል ሕግ ቁጥር 25 መሰረት የእምነት ክህደት ቃሉን በፍርድ ቤት ከማፅደቁ በፊት እዚህች ጠባብ ክፍል ውስጥ በተከሳሹ ስም በተከፈተ ፋይል ታሪኩን እያሰፈረ ነው፡፡

ግንቦት 22 ቀን 1997 ዓ.ም፡፡ ከተማዋ ከምርጫ ቀውሱ ወሬ ገና አላገገመችም፡፡ የአብዛኛው ህዝብ የወሬ ርዕስ ምርጫው በሆነበት የአብዛኛው ህዝብ የወሬ ርዕስ ምርጫ በሆነበት የአብዛኛው ፖሊስ ትኩረትም በዚህ ጉዳይ ላይ ባረፈበት በዚያ ወር ታገሰ በፖሊስ እጅ ወድቋል፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የዘጠኝ ዓመት ፍቅረኛውን በጩቤ ወግቶ ገድሏል መባሉ ነው፡፡

‹‹ዘጠኝ ዓመት ዘጠኝ ጊዜ ተሰቃይቻለሁ፡፡ ከዘጠነኛው ስቃይ በላይ የሚሸከም ልብ አልነበረኝም›› ይላል፡፡ ታሪኩን ለመርማሪው እየነገረው ነው፡፡ የተወለደው ከአዲስ አበባ ከተማ አዋሳኝ ቀበሌ አንዷ በሆነችው ዛሬ ግን በከተማው ውስጥ በተካተተችው ቂሊንጦ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ነው፡፡ ወደ መሀል ከተማ የገባው ደግሞ በ1988 ዓ.ም ሐምሌ ወር ላይ ነው፡፡ ወደዚህ ያመጣው ምክንያት እንጀራ ፍለጋ እንደሆነ ይናገራል፡፡ በአጎቱ በኩል ተፈልጎ የተገኘለትን የጥበቃ ስራ ለመስራት የአባቱን ሞፈርና ቀንበር ለታናሽ ወንድሙ አስረክቦ ቂሊንጦን ለቀቀ፡፡ ከዚያ በኋላ ነው የከተማ ልጅ የሆነው፡፡

አማርኛ ለመግባባት ያህል ብቻ የሚናገረውና ከተማውን እምብዛም የማያውቀው ታገሰ ጅማ ከአካባቢው ለመላመድ አልተቸገረም፡፡ ቀጣሪዎቹ ሰዎ ኦሮሞዎች መሆናቸው በቀላሉ ለመግባባትና ቀስ እያለም የከተማውን ህይወት ለመልመድ አስችሎታል፡፡ ባይተዋርነቱ ሲቀንስና ቀለል ሲለው አገሩ ሳለ የሚታወቅበትን ዘፈን ማንጎራጎር ጀመረ፡፡ ‹‹ምናለ ጥምቀት በመጣና የታገሰን ድምፅ በሰማን›› ይሉኝ ነበር ይላል ስለ ጓደኞቹ ሲናገር፡፡ በእርግጥም አሳዛኝ ቅላፄ ባለው ድምፅ የኦሮምኛ ዜማውን ሲያንቆረቁረው ጆሮን ለመያዝ ኃይል ነበረው፡፡ ከቀናት በኋላ በራሱ ቴፕ እየዘፈነ የቀዳውን ድምፁን በካሴት ማጠራቀምም ጀምሮ ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ አሰሪዎ ወጣ ሲሉ በር ላይ ተቀምጦ የሚያንጉራጉራትን ዜማ አጥብቃ የምትናፍቅ ሴት የተፈጠረችው ከሩቅ አልነበረም- ከዚያው ከግቢው እንጂ፡፡ የቤት ሠራተኛዋ፡፡ ታገስ ለአራት ዓመታት በዚያ ቤት ሲቆይ የዚህች ሴት ወዳጅ መሆኑን እንኳን ያወቀበት የገመተም አልነበረም፡፡ ልጁ ዘለግ ያለ ቁመናውና ፈርጠም ያለ ሰውነቱ ለጥበቃ ስራ ‹የሰጠ› ነው ያስብለው እንጂ ድምፁ ደግሞ በሌላ ወገን የማረካት ሴት አለች፡፡ ስራ በጀመረ በ6ኛው ወር ነበር መግባባት የቻሉት፡፡ እሱም ይህን ዘፈኑን እንደምትወድለት ስለሚያውቅ ባለቤቶቹ በሌሉት ወቅት ሲያንጎራጉርና የልጅቷን ልብ ሲያሸፍት ይውላል፡፡ የሚያዜመውን ነገር ቋንቋውን ሰምታ ረዳት ባትችልም የሆነ የሚያሳዝን ቅላፄ እንዳለው ግን ደጋግማ ትነግረዋለች፡፡ ታገሰ የጥበቃ ቤቱ ውስጥ በነበረችው ትንሽዬ ቴፕ ሁለቱ ቁጭ ብለው ሲያወሩ ደጋግሞ ቀርፆታል እንደምትወደው ነግራዋለች፡፡ እንደሚወዳት ነግሯታል፡፡ የሚዘፈነው ለእርሷ ብቻ እንደሆነም ጭምር፡፡ ይህ ድምፅ ለእርሷ ስጦታ ነው፡፡ የታገሰ ስጦታ፡፡

ትርጎን የወሎ ልጅ ናት፡፡ ሐይቅ አካባቢ ነው የተወለደችው፡፡ አዲስ አበባ ከመጣች ቆየት ብላለች፡፡ ከዚህ ቀደምም በሁለት ሶስት ሰዎች ቤት ተቀጠራ ሰርታለች፡፡ አሁን ከታገሰ ጋር ያገናኛት ቤት የገባችው ከአንድ ዓመት በፊት ቢሆንም ለቤቱ ግን የኖች የቤተሰቡ አባል ነው የምትመስለው፡፡ አየር ጤና አካባቢ በሚገኘው በዚህ መኖሪያ ቤት ብዙ ጊዜ እሷና ዘበኛው ታገሰ ብቻ የሚውሉባቸው ቀናት ብዙ ናቸው፡፡ ነጋዴው አባወራ ከባለቤታቸው ጋር ወደ ሱቃቸው ሲሄዱ ልጆቹ ደግሞ ወደ ትምህርት ቤታቸው ያዘግማሉ፡፡ ቤቱ አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር ቀን ላይ አይከፈትም፡፡ እንደተዘጋ በግቢው ውስጥ የሁለት ሰዎች ፍቅር እንደነገሰ ይውላል፡፡ ትርንጎና ታገሰ የሚለያያቸው ቅዳሜና እሁድ ነው፡፡ ያ እንደማይተዋወቁ እንደማይነጋገሩ እንደማይግባቡ ሆነው ሁለቱን የፈተና ቀን ከዓይንና ከጥርጣሬ ለመውጣት በመታገል ያሳልፉታል፡፡ ሁለት ቀን መታገሳቸው አምስት ቀን ያለስጋት ለመጫወታቸው መስዋዕት ናት፡፡ አንድም ሰው ሌላ ግንኙነት አላቸው ብሎ አስቦ አያውቅም፡፡

ትርንጎ ብዙ ጊዜ የምሽት ስራ ትወዳለች፡፡ ይህን የምታደርገው ሌሊቱ ገፋ ሲል ታገሰን ለመጎብኘት ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥርላት ነው፡፡ ይህን ሐሳብ ያመጣው ራሱ ቢሆንም የሌሊቱን ጨለማ ተግና ያቺን የዘበኛ ቤቱን በፍቅር አሟሙቃት የምትመለሰው ትርንጎ ግን ምን ማድረግ እንዳለባት ታውቃለች፡፡ አንዲት ከፉ ቀን መጥታ እስክታጋልጣቸው ድረስ ሁለቱ ጥንዶች ፍቅራቸውን ከብርድልብስ ከጣራና ግድግዳው ውጪ ለማንም ሹክ አላሉም ነበር፡፡

የቤቱ ወይዘሮ አንዲት ለነ ታገሰ የተረገመች በነበረችበት ዕለት ከምሽ 5፡30 ላይ አድርገውት በማያውቁት ሁኔታ ትርንጎን ፈለጓት፡፡ ተኝታ ይሆናል ብለው በማሰብ እንዳያስደነግጧት ብለው ወደምትተኛበት ሰርቪስ ክፍል ሄደው አንኳኩ፡፡ በሩ ክፍት በመሆኑ ውስጥ አለመኖሯን ለመመልከት አልተቸገሩም፡፡ በፍፁም ወደ ሌላ ቦታ ትሄዳለች ብለው ባለመጠርጠራቸው ሲያጧት ደንግጠው ነበር፡፡ የጥሪያቸውን ድምፅ ታገሰ ጥበቃ ቤት ውስጥ ተኝታ የሰማቸው ትርንጎ እየተንደፋደፈች በጨለማ ውስጥ ወደ ሰርቪስ ክፍሏ ስትጣደፍ ወይዘሮዋ ወደበረንዳው ሲመጡ እኩል ተገጣጠሙ፡፡ የምትሰጠው ምክንያትና በዚህ ሰዓት ከክፍሏ ወጥታ የነበረችበትን ቦታ ለመናገር የደረደረቻቸው ውሸቶች ወይዘሮዋን አላሳመኗቸውም፡፡ በዚህ ወቅት ነው ‹‹ከነገ ጀምሮ ጨርቅሽን ጠቅልለሽ ውጪ›› ብለው ያዘዟት፡፡

ያሉትን ተግባራዊ ለማድረግ አላመነቱም፡፡ ‹‹ነገ ተባብረሽ ቤቴን ታስፍሪዋለች እኔ በሌለሁበት እስከ ዛሬ ያደረግሽውን ነገርም አላውቅም›› በማለት ከቤት እንድትወጣ ጨከኑባት፡፡ ይህ ለታገሰ የማይጋፋው ጭንቀት ጣለበት፡፡ እሱም ተረኛ ተባራሪ እንደሆነ እየገመተ ባለበት ወቅት ወይዘሮዋ ስለድርጊቱ ሰብደውትና አስጠንቅቀውት እንዳይለመደው ነግረው ተዉት፡፡ እሱ ፍፁም ያሰቡት ነገር ልክ አይደለም ብሎ ቢናገርም ከማስጠንቀቂያ ያለፈ ቅጣት ሳይጣልበት ቀኗን ተሻገራት፡፡ ከዚያ ቀን ጀምሮ አካሉ ግቢ ውስጥ ቢሆንም ልቡ ግን ከትርንጎ ጋር ተሻግሮ ጠፋ፡፡

ከ2 ወራት በኋላ
ታገሰ ከዚህ በላይ መቆየት አልቻለም፡፡ ይህቺን ልጅ የወደደበት መንገድ ሌላ ማንንም መውደድ የሚችልበት መንገድ አይደለም፡፡ ዘወትር ስለርሷ እያሰበና እየተጨነቀ መኖሩ ፋይዳ እንደሌለው አውቋል፡፡ ስለዚህም ከዚህ ቤት ወጥቶ ትርንጎን መፈለግ እንዳለበት ወሰነ፡፡ ግን የት እና እንዴት እንደሚፈልጋት ማወቅ አልቻለም፡፡ ይህ በሆነበት አንድ ቀን ግን ያልጠበቀው ክስተት ተፈጠረ፡፡

እንደተለመደው የቤቱ ባለቤቶች ወደ ስራ ሄደዋል፡፡ ቤቱም ኦና ሆኗል፡፡ አዲስ የተቀጠረችው ሰራተኛ ከዚህ ዘበኛ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳይኖት ቀድሞ ተነግሯት ስለነበር በምግብ ሰዓት ምሳ እና እራቱን ጣል አድርጋለት ትመለሳለች እንጂ ብዙም ንግግር የላቸውም፡፡

ታገሰም ቢሆን ቀና ብሎ አይቷት አያውቅም፡፡ ለዚህች አዲስ ሴት ቀርቶ በዓለም ላይ አሉ ለተባሉ ቆነጃጅት እንኳን ገፁ የሚበራ አይመስለውም፡፡ በዚህች ቤቱ ውስጥ ያለርሱና ያለሰራተኛዋ ማንም በሌለበት ሰዓት ስልክ ተደወለ፡፡ የባለቤቶቹ ስልክ፡፡ ሰራተኛዋ እንደወትሮ እመቤቷ የደወሉ መስሏት ነበር ያነሳችው፡፡ ከወዲያኛው ጫፍ አንዲት ሴት ታገሰን እንደምትፈልግ ተናገረች፡፡ ሰራተኛዋ አንዳች ጥያቄ ሳታበዛ ታገሰን ጠራችው፡፡ ግራ ተጋባ፡፡ ስልክ ይፈልግሃል ሲባል ይህ የመጀመሪያው ነው፡፡ አንድ ሁለት ቀን የቤቱ ባለቤት ደውለው ትዕዛዝ ቢጤ ነግረውት ያውቃሉ፡፡ ከእሳቸው ሌላ የሚደውል አይኖርም ብሎ ፈጠን ፈጠን እያለ ወደ ሳሎኑ ገባ፡፡ ስልኩን ሲያነሳውና የደወለችው ሴት ትርንጎ ነኝ ስትለው ግን ማመን አልቻለም፡፡ ትርንጎ እዚህ ቤት በዚህ ሰዓት ማንም እንደማይኖር ታውቃለች፡፡ ለዚህ ነበር የደወለችበት አወሩ፡፡ በጣም ጠቂት ወሬ፡፡ በማግስቱ መምጣት ከቻለ ዑራኤል ቤተክርስቲያን በር ላይ እንደምትጠብቀው ገለፀችለት፡፡ ደስ አለው፡፡ ወትሮም ከዚህ ቤት ለመውጣትና እሷን ለመፈለግ የነበረው እቅድ አሁን ሳይለፋ ቤቱ ድረስ መጥቶለታል፡፡ እንደ ዕድል የቆጠረው ደግሞ የትም ሳይሄድ እሷ እራሷ ያለችበትን ማሳወቋ ነው፡፡ ቀድሞ ከስራ ባለመልቀቁ ተደሰተ፡፡
ምሽት ላይ ቆረጠ፡፡ ፈቃድ እንደሰጡት ሊጠይቅ ካልሆነም ደግሞ ጥሎ ሊሄድ፡፡ አሰሪው ሲመጡ በማግስቱ ወደ ቤተሰቡ ለራሱ ጉዳይ መሄድ እንደሚፈልግ ነገራቸው፡፡ አልተቀበሉትም፡፡ ቤቱን የሚጠብቅ ሰው ስለማይኖር ሰው በሚኖርበት ዕለት መሄድ እንደሚችል ነበር የነገሩት፡፡ እሱ ግን አልተስማማም፡፡ ሰውዬው ‹‹የተናገርኩትን ተናግሬያለሁ በቃ!›› በሚል አይት ጥለወት ገቡ፡፡

ነጋ፡፡ ታገሰ ሌሊቱ ግራ ገብቶት ነው ያለቀለት፡፡ ማለዳው አልመጣህ ብሎት ነው የነጋለት፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ታዲያ ሊነጋጋ ሲል የቀሰቀሱት እኚያ ሰውዬ ናቸው፡፡ አሰሪው ወደ ስራ ሲሄዱ ለምን ይህ ያህል ሰዓት ተኝቶ እንደሚያረፍድ አስጠርተው በስድብና በቁጣ ገሰፁት፡፡ ይህቺ ቃል ‹ሆድ ለባሰው› ታገሰ የመጨረሻው ሆነች፡፡ እሳቸው ባላሰቡት መንገድ ቤቱ ውስጥ ያለችውን አነስተኛ ሻንጣ አንስቶ ልብሱን ከታተተ፡፡ በኋላ አሰናብቱኝ አላቸው፡፡ አባረሩት፡፡ ሄደ፡፡ በዚያ ማለዳ ዑራኤል ቤተክርስቲያን አካባቢ ሲደርስ ልቡ ፍርሃት ፍርሃት እያለው ነበር፡፡ በፊት ለፊት በር ላይ ቆሞ እሷን በዓይኑ ይማትር ጀመር፡፡ ሳያስበው ከኋላው መጥታ ያዝ አደረገችው፡፡ ከዚያ በኋላ የነበራቸው ጓዜ ለሁለቱም ምን ያህል እንደሚዋደዱ ያሳየ ነው፡፡ ‹‹በእግራችን መገናኛ እስክንደርስ ድረስ ነው ያወራነው፡፡ ምን ያህል መንገድ እንደተጓዝን እንኳን አላወቅንም›› ይላል ታገሰ ለፖሊስ ሲናገር፡፡

ተለያዩ፡፡ እሱም ወደዘመዱ ቤት እሷም ወዳረፈችበት የአክስቷ ቤት፡፡ ከዚሁ ቀን በኋላ ያለውን ጊዜ ግን ሁለቱን ጥንዶች የሚለያያቸው ነገር አልነበረም፡፡

ከዓመታት በኋላ

ሁልጊዜ እሁድ እሁድ ሳይገናኙ ቀርተው አያውቁም፡፡ ታገሰ ከዘበኝነት ወጥቶ የቀን ስራ መስራት ከጀመረ በኋላ በየዕለቱ ትርፍ ጊዜ አለው፡፡ ትርንጎ ግን ያው በሰው ቤት ስለምትሰራ ሁሌም ከእሁድ በቀር የዓመት ፈቃድ የላትም፡፡ ስለሆነም ከእሁድ በቀር ከታገሰ ጋር ለመገናኘት ዕድሉ የለም፡፡ ፍቅረኞቹ ላለፉት 6 ዓመታት ያሳለፉት በርቀት ፍቅር ነው፡፡ ተገናኝተው ለማውራት ያለቻቸው ቀን ይህቺ ብቻ በመሆኗ እሁድን እንደነፍሳቸው ነው የሚሰስቷት፡፡ አብረው ለመኖር ግን የትርንጎ ፈቃድ አልተገኘም፡፡ እስካሁን ድረስ ታገሰ ቤት ተከራይቶ አብረው እንዲኖሩ ቢለምናትም በጄ አላለችም፡፡ ይህ ደግሞ የታገሰን አዕምሮ ወደ ሌላ ሃሳብ መርቶታል፡፡ ይህቺ ሴት ሌላ በፍቅር የምታስበው ሰው አለ ማለት ነው ብሎ፡፡ ድምፀ መልካሙ ታገሰ በድምፁ ያሸነፈው ልብ በሌላ ሰው የተጠለፈበት ስለመሰለው ተናዷል፡፡ አብረው ለመኖር ደጋግሞ ሲጠይቅ የምትሰጥ ምላሻም እርሱ በሚፈልገው መልኩ ባለመሆኑ ደስታ ርቆታል፡፡ ወደፊትም አጋጣሚ ቢፈጠርላት ከእርሱ ለመለየት ቀን የምትጠብቅ አድርጎ ሳላት፡፡ ፈርዶበት ቅናት ላዩ ላይ ሰፈረ፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላም በመካከላቸው የነበረው ግንኙነት ሻከረ፡፡

በአጓጉል ፀባዩ የሚጨቀጭቃትን ይህንን ሰው ልትቋቋመው አልቻለችም፡፡ ብስጭቷ ገንኖ ወጥቷል፡፡ አልፎ አልፎ ትናገረዋለች፡፡ ያቺ ስንት ነገር የሚያሳልፉባት እሁድ በየሳምንቱ የጭቅጭቅ ሆኗል፡፡ ይህ ደግሞ ትርንጎን ቅር አሰኝቷታል፡፡ ታገሰ ያለመፈለግ ስሜት ከተሰማው ቆይቷል፡፡

‹‹ያለፉትን ዓመታት ሙሉ ለእርሷ ስል ብዙ መስዋዕትነት እንደከፈልኩ ታውቃለች፡፡ ከስራ ወጥቼ ተንከራትቻለሁ፡፡ ሰርቼ የማገኘውን ነገር ሁሉ ለእርሷ አስፈላጊ ነገር በመግዛት ገንዘቤን አጥፍቻለሁ፡፡ ቤት ተከራይ ብላኝ ተከራይቻለሁ፡፡ የቤት ዕቃ ግዛ ብላኝ በአቅሜ መጠን ገዝቻለሁ፡፡ ትርንጎ የተቀጠረችው ሀብታም ቤት ስለሆነ እዚያ ያየችው ነገር እንዲሟላላት የፈለገች መስላለች፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ግን እኔን ለማዘናጋት እንጂ እንደማታገባኝ ታውቃለች፡፡ በተለይ እኔን አጃጅላ ሌላ ሰው እንደፈለገች ገብቶኛል›› ብሏል ለፖሊስ ሲናገር፡፡

የዚህ ሰው ልብ በፍቅረኛው ላይ አምርሯል፡፡ አለችኝ የሚለው ነገር ዛሬ ፖሊስ ጣቢያ ለመጣው ጉዳይ መሰረት እንደሆነበት ይገልጻል፡፡ ላለፉት 8 ጊዜያት የቋጠርኳቸው ቂሞች በርሷ ታይተውኛል የሚለው ይህ ‹አፍቃሪ› የትርንጎ ሀጢያት ናቸው የሚላቸውን ነገሮች ዘርዝሮ ተናግሯቸው ነበር፡፡

‹‹ስልክ ደውይልኝ ስላትም- ያለሽበት ቤት ስልክ ልደውል ስላትም እሺ አትልም፡፡ ፍቅረኛ እንዳላት እንዲታወቅ አትፈልግም፡፡ እንደር ስላት ‹አዳር ፈቃድ ላንተ ብዬ ያለባህዬ አልወስድም› አለችኝ፡፡ እኔ ለእርሷ ብዬ ስንት ነገር ስሆን እሷ ለእኔ ብላ ማደር አልፈለገችም፡፡ አንድም ቀን እወድሃለሁ አላለችኝም፡፡ እኔ ስጠይቃት ብቻ ነው የምትመልስልኝ፡፡ ቤቴ ነይ ስላት ሁለት ቀን ብቻነው የመጣችው፡፡ ‹ያላገባሁት ወንድ ቤት ለምን እሄዳለሁ› አለችኝ፡፡ ይህም በእኔ ላይ አለመተማመኗን መሰከረልኝ፡፡ ዘመዷን እንድታስተዋውቀኝ ስጠይቃት እምቢ አለች፡፡ ታፍርብኛለች ማለት ነው፡፡ ከእኔ ሌላ ሰው ማፍቀር ትችያለሽ ወይ ብዬ ስጠይቃት ‹ሰው እኮ ነኝ› አለች፡፡ ከእኔ ስትለይ ግድ የላትም ብዬ አሰብኩ፡፡ የእኔን ቤተሰብ ላስተዋውቅሽ ስላት ‹ይቅርብኝ› ያለችኝ ስለምትንቀኝ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም አገር ቤት እያለች ያገባችውንና አምልጣው የመጣችውን ባሏን ሁለት ቀን አነሳችብኝ፤ ትፈልገዋለች ማለት ነው፡፡ እነዚህ ስምንት ነገሮች ለዓመታት የቆየበትን ፍቅር ንደውብኝ ኪራ ደርሶብኛል፡፡ ያቃጠልኩት ጊዜ ቆጭቶኛል፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ ላናግራት ወስኜ ቤቴ ይዣት ስሄድ ግን ያ ዕለት ያላሰብኩት ሆነብኝ›› ብሏል፡፡ እነሆ ዘጠነኛ ስቃይ ያለውን ታሪክም ተናገረ፡፡

ግንቦት 19 ቀን 1997

ታገሰና ትርንጎ ቤት ተቀምጠዋል፡፡ ዛሬ ይዟት የመጣው አንድ ጥያቄ ሊጠይቃት ነው፡፡ ‹‹ትፈልጊኛለሽ አትፈልጊኝም?›› የሚል፡፡ እፈልግሃለሁ ካለች እንድታገባው፤ አልፈልግህም ካለች ትታው እንድትሄድ ነበር ውሳኔው፡፡ ቀትር ላይ ነው በሰበብ ያስመጣት፡፡ ለቅሶ አለብኝ ብላ ፍቃድ ጠይቃ ነው የመጣችው፡፡ እዚያች ሳሳ ቤት ውስጥ ተቀምጠው ብዙ ሳይቆዩ ወሲብ እንዲፈፅሙ ጠየቃት፡፡ ፈቃደኛ አልሆነችም፡፡ ምክንያቱም ደግሞ እሱ እንደሚናገረው ‹‹አረግዛለሁ›› የሚል ነው፡፡ እሱ ግን በሌላ ተርጎሞታል፡፡ አልፈልግህም ማለትሽ ነው ሲላት ‹‹እንዲያ ከመሰለህ አዎ›› አለችኝ ብሏል፡፡ ይህ ደግሞ ለታገሰ ‹‹ዘጠነኛው ስቃይ ነው›› ተናደድኩ ይላል፡፡ ለፖሊሱም የነገረው ይህንኑ ነው፡፡

‹‹ይህንን ቃል ስትናገረኝ ወረረኝ፤ ያቃጠልኩት ዕድሜ ቆጨኝ፡፡ በወጣትነቴ ስንት ዕድል ነበረኝ፡፡ ዛሬ ብቻዬን አልኖርም ነበር፡፡ በዓይኔ ባላይም የካደችኝ መሆኑን ሰውነቴ ነግሮኛል፡፡ ይህን ደግሞ ማረጋገጥ አያስፈልገኝም፡፡ ከዚህ በኋላ የማላውቀው ስሜት በውስጤ ገባ፡፡ ሰይጣን አሳሳተኝ፡፡ ስለዚህም ገደልኳት››

ታገሰ ይህቺን ወጣት የገደላት ፍራሹ ስር ደብቆት በነበረው ጩቤ ነው፡፡ ዘጠኝ ጊዜ የተለያዩ የሰውነቷ ክፍል ላይ ወግቷታል፡፡ ደሟ ያንን አልጋ ሙሉ በሙሉ ደም ሸፍኖታል፡፡ ታገሰ ‹‹የዘለዓለም ፍቅረኛዬ›› ያላትን ሴት ሲያብሰለስለው በነበረው ውሳኔ በጩቤ ከገደላት በኋላ ለፖሊስ እጁን ሰጠ፡፡ ያደረገው ነገር ትክክል ባይሆንም ሌላ ምርጫ አልነበረኝም ብሏል፡፡ ፍፁም የተሳሳተ ውሳኔ መሆኑን ግን ልቦናው ያውቃል፡፡ ታገሰ ወደ ወህኒ ቤት ሲወርድ ግን ፖሊስ ጋር የሰጠው ቃል በአፉ ውስጥ አልነበረም፡፡ ይልቅስ ለቅሶ ፀፀትና ናፍቆት እያንገላቱት ነበር፡፡ ‹‹እሷን ከምገድል ራሴን ገድዬ ቢሆን ምንኛ ጥሩ ነበር›› ብሏል፡፡

The post ‹‹ዘጠነኛው ስቃይ›› – (እውነተኛ የወንጀል ታሪክ) appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2784

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>