አርቲስት ሰብለ ተፈራ አዲስ አበባ ውስጥ ዛሬ 8 ሰዓት አካባቢ ከጎተራ ወደ ሳሪስ ጎዞ ስታደርግ ንፋስ ስልክ ቀለም ፋብሪካ አካባቢ በደረሰባት የመኪና አደጋ ህይወቷ ማለፉን መዘገባችን ይታወሳል:: መኪናውን ያሽከረክር የነበረው ባለቤቷ ሞገስ ሕይወቱ ተርፏል:: የሰብለ ሕይወትን የሚያስቃኘውና በቅርቡ አሜሪካ መጥታ በነበረበት ወቅት ከባውዛ ጋዜጣ ጋር አድርገው የነበረውን ቃለምልልስ ለትውስታ እናስነብባችሁ::
በቲያትር መድረክ ስራዎች ከኢትዮጵያ ውጭ እየተንቀሳቀስሽ ነው?
አዎ፡፡ አሜሪካ ግን ስመጣ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ በአሜሪካ በተለያዩ ስቴቶች “የእኛ እድር” የሚል የመድረክ ድራማ ለማሳየት ግብዣ ተደርጎልኝ ነው የመጣሁት፡፡ የቲያትሩ ደራሲ መልካሙ ዘሪሁን ይባላል፡፡ ኢትዮጵያ እና እንግሊዝ አገር የተሰራ ቲያትር ነው፡፡
ከቲያትር ይልቅ የሙዚቃ ስራዎች ከኢትዮጵያ ውጪ በተለያየ የዓለም ክፍሎች ይታያሉ?
ቲያትር ትልቅ ወጭ አለው፡፡ እንኳን በዚህ ደረጃ የክፍለ ሃገር እንቅስቃሴም በጣም ቀንስዋል፡፡ ድሮ ቲያትር ያለ ስፖንሰር የሚሰራ ስራ ነበረ፡፡ የተዋናይ ክፍያ ትንሽ ነው፤ አበል ትንሽ ነው፡፡ አሁን ግን ሁሉ ነገር ውድ በመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥም የምንቀሳቀሰው በስፖንስር ነው። ነገር ግን ከሁለትና ከሶስት ቲያትሮች ያልበለጠ ቲያትር ከኢትዮጵያ ውጭ ተጉዝዋል፡፡
የቲያትር ተመልካች ይለያል፡፡ ምን አልባት ቲያትር የሚመለከት ሰው የሙዚቃ ኮንሰርት ማያይ ወይንም የማያደምጥ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዴም ደግሞ ሁለቱንም የሚያይ ሊሆን ይችላል፡፡ የቲያትር ተመልካች ልዩ ነው፡፡ በቲቪ የሚያየውን ሰው በአካል መድረክ ላይ ማየቱ በራሱ ልዩ ነገር ይፈጥርለታል፡፡ ጉጉት፣አድናቆት አለ፡፡ በተዘዋወርኩባቸው የዓለም ክፍሎች የቲያትር ተመልካች ደስተኛ ሆኖ አዳራሽ እየሞላ ከተሰጠው ቀን ውጭ ተጨማሪ ቀን እየሰራን ነው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰን የምንሄደው፡፡ እንቅስቃሴው አለ፡፡
በቲያትር ስራዎች ወደየት ሃገሮች ተጓዝሽ?
በተዋናይነትና በረዳት አዘጋጅነት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተዘዋውሪያለሁ፡፡ በዓለም ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ፕሮሞቶሮች “የትኛው ቲያትር ለተመልካች ይሆናል?”
በሚል ተመልክተው እና አጥንተው ገበያቸውን አማክለው የመረጡት ቲያትር ላይ ካስት ተደርጌ ተጉዣሁ፡፡ እንግሊዝ፣ ሳውዝ አፍሪካ፣ እስራኤል፣ ግሪክ፣ ሱዳን፣ አሜሪካ … ሃገሮች በተለያዩ ቲያትሮች ተጉዣለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ካናዳ፣ ኳታር፣ ዱባይ ሌሎች ሃገሮች ካሉ ፕሮሞቶሮች ጋር ለመስራት እየተነጋገርን ነው፡፡ በተለይም ወደ ኢትዮጵያ ከተመለስኩ በኋላ ከሌሎች አርቲስቶች ጋር ለመጓዝም በእቅድ ላይ ነን፡፡
የመጀመሪያውን ጉዞ ለንደን ላይ ካደረኩ በኋላ ተመልካቹ ለቲያትር ያለውን ፍቅርና አድናቆት ሳይ ከመድረክ የወረዱ በርካታ ቲያትሮች አስብኳቸው፡፡ በተለይም የሃገራችን ኪነጥበብና ቲያትር ለማሳየት መድረኮች ቢፈጠሩ ሁሉ ብዬ ነው የተመኘሁ፡፡ ይህንንም ማለቴ የአገራችንን
ባህል የሚያሳዩ የገጠሩን ክፍል የሚያስቃኙ ቲያትሮች ከኢትዮጵያ ከወጡ ብዙ ዓመት የሆነቸው ቢያዩት ብዬ እመኛለሁ፡፡ ተሰርተው የወረዱ ጥሩ ጥሩ ቲያትሮች አሉ ከፕሮሞተሮች ጋር እየተነጋገርኩ ነው፡፡
“የፍቅር ካቴና” “ግይድ” የሚባሉ ቲያትሮች አሉ፡፡ ኮሜዲ አስተማሪ አገራችን ላይ ያለውን ትክክለኛ ነገር የሚንጸባርቅ፣ የባለገሩን ህይወት የሚያሳዩ እነ ባቢሎን በሳሎን ከመድረክ የወረዱ ሌሎች ቲያትሮች ከኢትዮጵያ ወጥተው የመታየት እድል ቢኖራቸው በውጭ የሚኖረው ተመልካች ደስተኛ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሚሸቱ ቲያትሮች አሉ፡፡ የሚናፈቁ የትወና ጥበባቸው፣ አዝናኝና አስተማሪ የሆኑ በጥቂት ሰዎች የሚሰሩ ቲያትሮች፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ይደረግ ከነበረ ጉዞ አለምን መዞር
ተጀመረ ማለት ነው?
አዎ፡፡ አዲስ አበባ ያሉ ቲያትር ቤቶች፣ ትምህርትቤቶች ከዚያም በመላ ኢትዮጵያ ተዘዋውሪያለሁ፡፡ ቲያትር በጀመርኩ ወቅት፣ የከተማ አውቶብስ አስራ አምስት ሳንቲም በነበረ ጊዜ ነበር፡፡ ከጎተራ ጊወርጊስ ድረስ አስራ አራት ቁጥርን ይዤ እሄዳለሁ፡፡ ሰላሳ ሳንቲም ከተሰጠኝ ለእኔ ደስታ ነው ደርሶ መልስ፡፡ ሞያዬን እናቴም አባቴም አይወዱትም ነበር፡፡
“ግጥም ላነብ በትምህርት ቤቴ ተመርጬ ልሄድ ነው” ብዬ ቲያትር ለመስራት ሰላሳ ሳንቲም ተቀብዬ እሄድ ነበር አንዳንድ ጊዜ እናቴ ደሞዝ ስትቀበል የአንድ ሳምንት ትኬት በብር ከሃምሳ ሳንቲም ትኬት ትቆርጠልኝ ነበር አልፎ አልፎም በቤት ውስጥ ስራ ሰራቼ ያስደስትኳት ጊዜ ሳንቲም ተሰጠኛለች፡፡ እሷን እቆጥባለሁ፡፡ ካልሆነም ቲያትር ቤት የማገኛቸው ጓደኞቼን አምስት አምስት ሳንቲም ለምኜ ወደ ቤቴ እመለስ ነበር፡፡ ሳንቲም ከሌለን ደግሞ ከጊዎርጊስ እስከ ጎተራ ድረስ በእግራችን እንሄዳለን – እንቁጣጣሽ ከምትባል ጓደኛዬ ጋር፡፡ አልፎ አልፎም የአውቶብስ መጠበቂያ ስፍራ እቆምና ከአውቶብሱ የሚወርድ ሰው ጉዞውን ጨርሶ ሲወርድና ትኬት ጣል ሲያደርግ፣ የጣለውን አንስቼ አውቶብሱ ውስጥ እገባለሁ፡፡ በአውቶብሱ ውስጥ ተቆጣጣሪ ይዞኝ ጆሮዬን ቆንጥጦኛል፡፡
የመጀመሪያ ደሞወዝሽ ስንት ነበር?
ኢትጵዮጵያ ሬድዮ ለ“አውደ ገጠር” ፕሮግራሙ ድራማ ሰርቼ ሃይ ብር ተከፍሎኛል፡፡ በቀጣይ አንድ ስራ ሰርቼ መቶ ሃይ ብር ሲከፈለኝ ስልሳ አምስት ብር አውጥቼ ለእናቴ ሽቶ ገዛሁ፡፡ በብዛትም ችግሬ የአውቶብስ ትኬት ስለነበረ በርከት አድርጌ መግዛቴን አስታውሳለሁ፡፡በትምህርት
ቤት ሚኒ ሚድያ ውስጥ የተጀመረ ጋዜጠኛ የመሆን ፍላጎት እና ተሳትፎ ነው ወደ አርቲስትነት ያሸጋገረኝ፡፡ በእረፍት ሰዓትና ጠዋት ዜና አነብ ነበር፡፡ አልፎ አልፎም በአንድ ክፍል ውስጥ ለምንማር ተማሪዎች አስተማሪዎቻችን አስተምረውን ከክፍል ሲወጡ ዴስክ ላይ በመውጣት አስተማሪዎችን በመምሰል እቀልድ ነበር፡፡ በተለያዩ ቋንቋዎች በመቀለድ፣ በማስመሰል እጫዎትላቸው ነበር፡፡ እንዳጋጣሚ አንድ ጓደኛዬ ፋዘር/ተስፋዬ አበበ/ ጋር ይዛኝ ሄደች፡፡ ሳይ መድረክ ላይ ቲያትር እየተለማመዱ ነው። ከዚያን ቀን ጀምሮ ጋዜጠኝነቱ ቀረና ተዋናይ ሆንኩ። ሃያ ዓመታት አለፈ በዚህ ሁኔታ እንግዲህ፡፡ በነገራችን ላይ ጋዜጠኝነቱንም አልተወውም፡፡ እንደ ጋዜጠኛ የአየር ሰዓት ወስጄ ለመስራት እየተንቀሳቀስኩ ነው፡፡ መጻፍ ከሆነ ግጥም እጽፍ ነበር፡፡ አንድ ቀን ግጥሞቼን ሰብስቤ አሳትማለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ አሁን አሁን ደግሞ መድረክ እየመራሁ ነው፡፡ አንድ ቀን ደግሞ የጋዜጠኝነት ካራክተር ለመጫወት ፍላጎት አለኝ፡፡
ወቅቱ ፋሲካ ነው፣ ለቤተሰብ ለአውዳመት የሚያስፈልገውን አሟልተሸ ነው የመጣሽ?
ትዳር ይዤ እስከምወጥበት ጊዜ ድረስ ያለው በቤተሰብ ውስጥ አገልጋይ ትጉ ሰራተኛ ነበርኩ፡፡ የጉልበት ስራ ሳይቀር ባለሞያ ነበርኩ፡፡ ልብስ ማጠብ፣ አትክልት መኮትኮት…. የመሳሰሉትን፡፡ ከቤት አልፌ የተከራይ ቤቶችንም ልብስ፣ ልጆቻቸውን አጥብ ነበር፡፡ በዚህም እገረፍ ነበር፡፡ አሁን እንደ ድሮው አይደለም ስራ ቢዚ አድርጎኛል፡፡ ምን አልባት የበዓል ዕለት ሁሉ ቤት ላልውል እችላለሁ፡፡
የበዓል ዝግጅት፣ መድረክ መምራት፣ ጭውውት ሊኖረኝ ይችላል። አሁን ባለሁበት ደረጃ ቤትም ላልውል እችላለሁ:: ነገር ግን ለበዓል ቤት ከዋልኩ በቤት ውስጥ የምትሰራልኝ አለች አጋዥ አግኝቻለሁ አብረን እንሰራለን፡፡
አርቲስቶች ዓመት ባህልን በቤት ውስጥ አያከብሩም፣ አንችም ይሄው ፋሲካን በስራ ላይ እያሳለፍሽ ነው?
ፋሲካ ስትይ አንድ ነገር አስታወሽኝ፡፡ የመጀመሪያ መድረክ ስራዬ ነው፡፡ ገና ቲያትር ስጀምር የፋሲካ እለት አቃቂ ከተማ ቲያትር እናሳይ ነበር፡፡ የበዓል እለት እኛ ቤት አይወጣም…አይደለም ፋሲካ ስራና ትምህርት ከሌለ ከቤት አይወጣም፡፡ ፕሮግራም ተዘርግቶ አትሄጅም ተባኩ፡፡ መሪ ተዋናይ ነኝ። ከሁለትና ሶስት ወር በላይ ነበር ልምምዱን ያደረግነው፡፡ በዓመት በዓል ከቤት መውጣት የማይታሰብ ነው አይቻለም ተባለኩ፡፡ በህይወቴ እንደዛ ቀን አልቅሼ አላውቅም፡፡ ለቴዎድሮስ ተስፋዬ ወጥቼ ደወልኩለትና እናቴ ከቤት አትወጭም ተብያለሁ አልኩት:: ቴዲ ደወላላት
ነገራት፡፡ እነ ቴዲ ጋር እስከደርስ አላመንኩም እያለቀስኩ ነው የሄድኩት፡፡የዛሬ አስራ ስምንት ዓመት ነው በፋሲካ እለት ቲያትር ይዘን ወደ ጅማ እንሄድ ነበር፡፡ ቲያትር እየሰራን ከመድረክ ጀርባ ሴቶች ሽንኩርት እንከትፋለን፣ እናቁላላለን… ቲያትሩን ስንጨርስ የተቁላላውን ሽንኩርት ወደ አረፍንበት ሆቴል ይዘን ሄደን ዶሮውን ገነጣጥለን ሰርተን እንደ ደንቡ ለሊት ዘጠኝ ሰዓት ተነስተን ገደፍን… ፆመኙቹን አስፈታናቸው፣ ዓመት በዓልን አከበርን በዛው እለት የማልረሳው ቅቤ አንጥረን በብልቃጥ አስቀምጠን ነበር ከመድረክ ጀርባ … ሜካፕ ነበር የሽማግሌ(ጸጉርን ሽበት)ሚያስመስሉ…አንዱ ልጅ ጥንቁል አድርጎ ሽበት ለማስመሰል ተቀባው…ሺሸተው ነው የወጥ ቅቤ ሽበት ለማስመሰል እየተቀባ መሆኑን ያወቀው፡፡
በአንድ ወቅት ደግሞ “የሰው ሰው” የሚል ቲያትር ይዘን ወደ አስመራ ስንሄድ ታመምኩኝ፡፡ ለካ ባህር ዳር ነው ወባ የያዘኝ፡፡ መድረክ ላይ እየተደገፍኩ እንደሰራሁ ትዝ ይለኛል፡፡ “መድረክ መድሃኒት ነው” እንላለን እውነት ነው:: ልክ ከመድረክ ከወጣን በኋላ ግን ምን እያደረኩ እንደሆነ አላውቀውም ነበር፡፡ ከሰዓታት በኋላ ግን ብንን ስል ብዙ ሰው የተኛበት መካከል ነኝ፡፡ ነቅቼ ስመለከት ለአራት ቀን እንድተኛ ተጽፍዋል፡፡ ተዋናያኖቹ ያለ ስራ መቆየት ከባድ ነው። አበል፣ የመኪና ኪራይ ሁሉ ስላለ በቃ ወደ አዲስ አበባ እንመለስ የሚል ሃሳብ ቀረበ፡፡
በአውሮፕላን ብቻዬን ልላክ ነበር፡፡ ነገር ግን እሰራለሁ አልኩኝ፡፡ ጉሉኮሴን ወስጄ ጠነከርኩ ተነስቼ መድረክ ሰራሁ፡፡
ቤተሰብ ያወጣልሽ ስም እየተዘነጋ ነው?
አዎ:: ማንም ሰው ብቅ ስል “ትርፌ” ይሉኛል:: አንዳንዶቹ “ሰንሺ” ይሉኛል:: “ትርፌ” ብለው ሲጠሩኝ አቤት እላለሁ:: በሄድኩበት አገር ሁሉ እንደ ስጦታ ዳቦና አበባ ነው የሚሰጡኝ፡፡
በቀጣይ ምን እንጠብቅ?
“አልበም” የሚል ፊልም አለኝ ድርሰቱን ገዝቸው ነው አሳያለሁ የሚል እቅድ አለኝ፡፡ በሰብለ ፊልም ፕሮዳክሽን አማካኝነት ፕሮዲዩስ ያደረኩት እኔ ነኝ፡፡ እዚህ ያለኝን ከጨረስኩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ስሄድ በሰብለ ፊልም ፕሮዳክሽን የሚሰራ የሬድዮ ፕሮግራም የአየር ሰዓት ይዤ መስራት እቅድ አለኝ፡፡
መልካም የስራ ዘመን፣ መልካም የፋሲካ በዓል ይሁንልሽ፡፡ ለመላው የክርስቲያ እምነት ተከታዬች በመሉ እንኳን ለፋሲካ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፡፡ ለአድናቂዎቼ እወዳችኋለሁ፡